Fana: At a Speed of Life!

ዓድዋ የአፍሪካዊያን የትግል አርማና የመንፈስ ጥንካሬ ምንጭ በመሆኑ አስተሳሳሪ ቅርሳችን ነው – አገልግሎቱ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓድዋ በኅብር የጸናች ሀገርን ለመፍጠር መሠረት የጣለና አሁንም የትውልዱ አሻራ ሆኖ የታላቋን ሀገር ትልቅ ስዕል የሚያሳይ የታሪካችን ዋነኛ ምዕራፍ ነው ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

አገልግሎቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ÷ ዓድዋ የማይደፈረውን የቅኝ ገዥዎችን የበላይነትና ፍላጎት መና ያደረገ፣ የታሪክ አንጓ ነው ብሏል፡፡

ዓድዋ ድላችንም ቅርሳችንም ነው ያለው አገልግሎቱ÷ ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት፣ የአፍሪካዊያን የትግል አርማና የመንፈስ ጥንካሬ ምንጭ በመሆኑ አስተሳሳሪ ቅርሳችን ነው ሲል ገልጿል፡፡

የአገልግሎቱ መግጫ ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡፡

ዓድዋ ድላችንም ቅርሳችንም ነው!

*****************

ኢትዮጵያ ጠንካራ ሥርዓተ መንግሥትና የጥንታዊ ሥልጣኔ ማዕከል ከነበሩ ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡ በዚህ ረዥም የታሪክ ጉዞ ኢትዮጵያ ሀገራችን ባሳለፈቻቸው የታሪክ ምዕራፎች ሁሉ ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን ለመጣስ ተከታታይ ወረራዎች ተፈጽመውባታል።

ይሁን እንጂ የተቃጡባትን ወረራዎችና ጦርነቶች በአኩሪ ተጋድሎና መስዋዕትነት በመመከት የዓለማችን የነፃነት ቀንዲል ለመሆን በቅታለች። ሕዝቦቿ የሰውን ሀገር ግዛት ወርረው የማያውቁና የራሳቸውንም ስንዝር መሬት ሳያስደፍሩ በአያሌ መስዋዕትነት ውስጥ አልፈዋል።

ዓድዋ ኩሩ ሕዝብ እና ነፃ ሀገር ያስረከበን የነጻነትና የድል ሰንደቅ ነው፡፡ ዓድዋ በሁሉም ኢትዮጵያውያ ደምና አጥንት የተገነባ የተጋድሎና የአይበገሬነት ዓርማ ነው፡፡ የዓድዋ ድል አባቶቻችን ለሀገራቸው ክብር ያለአንዳች ልዩነት በጋራ ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ድል ያጎናፀፉን ብቻም ሳይሆን የወል እውነቶቻችንን በጠንካራ አለት ላይ እንዲገነቡ ያደረጉበት ድል ነው፡፡ በመሆኑም ዓድዋ ለእኛ ድልም ቅርስም ነው፡፡

ዓድዋ በህብር የጸናች ሀገርን ለመፍጠር መሠረት የጣለና አሁንም የትውልዱ አሻራ ሆኖ የታላቋን ሀገር ትልቅ ስዕል የሚያሳይ የታሪካችን ዋነኛ ምዕራፍ ነው፡፡ ዓድዋ የማይደፈረውን የቅኝ ገዥዎችን የበላይነትና ፍላጎት መና ያደረገ፣ የታሪክ አንጓ ነው። ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት፣ የአፍሪካዊያን የትግል አርማና የመንፈስ ጥንካሬ ምንጭ በመሆኑ አስተሳሳሪ ቅርሳችን ነው፡፡

ዓድዋ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በሀገር ፍቅር ገመድ ያሰናሰለ፣ የሀገር ሉዓላዊነትን ከአካባቢያዊ ልዩነት ያስቀደመ የነፃነት ብስራት ሲሆን፤ ለጠላቶቻችን ደግሞ ሀፍረትን ያከናነበ የኢትዮጵያ ህብረብሔራዊ አንድነት የጸናበት የማእዘን ድንጋይ ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ በመሐል ፒያሳ የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ፕሮጀክትም የዚሁ የወል እዉነት ዋና አካል መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ፕሮጀክቱ የዓድዋ ድልን በሚመጥን ደረጃ ተገንብቶ ለእይታ መብቃቱ የጋራ ድሎችንን በማጉላት፣ ከፋፋይ ትርክቶችን በዘላቂነት በማክሰም የወል ትርክቶች እንዲገነቡና ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ በማድረግ የኢትዮጵያን ህብረ ብሔራዊ አንድነትና ወንድማማችነት ስር እንዲሰድ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን ብቻም ሳይሆን ለጥቁር ሕዝቦች የትግል አርማና የመንፈስ ጥንካሬ ምንጭ ነበር፡፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያ የአፍሪካ መዲና በሆነችዉ አዲስ አበባ እምብርት መገንባቱ ለኢትዮጵያውያን መታሰቢያነት ብቻም ሳይሆን ለነፃነታቸው ለታዋደቁ አፍሪካያን ወንድሞችም ጭምር መሆኑን ያሳያል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባችን፤ የአፍሪካ ድል የሆነውን የዓድዋ ድል የሚዘክር ፕሮጀክት እውን ማድረጓ ያላትን አፍሪካዊ ዕሴት የበለጠ ያጎላዋል።

ፕሮጀክቱ እንደሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ሁሉ የጀመርነውን እንደምንጨርስ፣ ቃል የገባነውን በላቀ ጥራት እንደምንፈፅም የሚያመላክት ሌላኛው ምስክር ነው። የፕሮጀክቱ እውን መሆን ኢትዮጵያ ትልቅ ዓልማ እንደምትፈጽም የሚያመላክት ስኬት ነው።

በተጨማሪም ይህ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥቅማቸው የሚከበረው በመተባበር እንጂ በመለያየት እንዳልሆነም ያሳየ የወል ምልክታችን ነው። ታላቁ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዚህ መልኩ መጠናቀቅና ለምርቃት መብቃት ለጊዜያዊ ችግሮች እጅ ሳንሰጥ ትላልቅ ሀገራዊ ትልሞቻችንን እንደምናሳካ አስረጂ ድላችን ነው፡፡

ለከፋፋይ ትርክቶች ሳንረታና ሳንበረከክ የወል ትርክቶቻችንን አፅንተን በዓድዋ ድል ዕሴቶች በጋራ ተንቀሳቀስን ጠንካራና የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ የሚያስቆመን ምድራዊ ኃይል እንደሌለ የዓድዋ ድላችን ማሳያ ነዉ፡፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ፕሮጅክትም ይሄንን ታላቅ ድል የምንዘክርበት እና ለትዉልድ የምናሻግርበት ታሪካዊ መዛግብታችን ነዉ፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.