Fana: At a Speed of Life!

ኢራቅ በአሜሪካ የሚመራው ጥምር ተልዕኮ እንዲያበቃ የሚደረገው ውይይት መቀጠሉን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የሚመራው ዓለም አቀፍ ጥምረት በኢራቅ ያለውን ተልዕኮ ለማስቆም አዲስ ዙር ውይይት መቀጠሉን የኢራቅ መንግስት አስታውቋል።
 
የኢራቅ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ራሶል÷ወታደራዊ ሁኔታን፣ በአሸባሪ ቡድኑ የሚደርሰውን ስጋት ደረጃና የኢራቅ ሃይሎችን አቅም ለመገምገም ከጥምረቱ ጋር ስብሰባ መጀመሩን ተናግረዋል።
 
ራሶል እንዳስታወቁት÷በስብሰባዎቹ በመመስረት በኢራቅ ውስጥ ያሉ የህብረት አማካሪዎች ቀስ በቀስ የሚቀንሱበት የጊዜ ሰሌዳ ይዘጋጃል፡፡
 
ይህም በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሰውን የሽብር ቡድን የመዋጋት የትብብር ተልእኮ እንዲያበቃ እና ኢራቅ ከጥምረት ሀገራት ጋር ወደ ሚኖራት የሁለትዮሽ ግንኙነት እንድትሸጋገር ያስችላል ብለዋል።
 
በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በሀገሪቱ በሚገኙ የአሜሪካ ሰራተኞች ላይ ታጣቂ ቡድኖች የሮኬት ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ አሜሪካ በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች ላይ ኢላማ ያደረገ ጥቃት መፈፀሟ ይታወቃል፡፡
 
ይህም የአሜሪካ ወታደሮች ከሀገሪቱ በፍጥነት መውጣትን የተመለከቱ ንግግሮች እንዲፋፋሙ ማድረጉ ነው የተመላከተው፡፡
 
የሚያደናቅፍ ነገር እስከሌለ ድረስ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ከጥምረቱ ጋር የሚደረጉት ስብሰባዎች በየጊዜው እንደሚካሄዱም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
 
ከዚህ በፊት በኢራቅ ያለውን የትብብር ተልዕኮ ለማስቆምና ኢራቅ ከጥምረቱ ሀገራት ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ የደህንነትና ወታደራዊ ደረጃዎች ለማሸጋገር ከአሜሪካ ጋር መስማማቷን ሲጂቲኤን በዘገባው አስታውሷል፡፡
 
 
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.