Fana: At a Speed of Life!

ግለሰብን አሳፍረው በመውሰድ ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርገዋል የተባሉ ተከሳሾች በእስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንገድ ዳር ቆማ ታክሲ በመጠበቅ ላይ የነበረችን ግለሰብ በባለሶስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) አሳፍረው በመውሰድ ንብረቷን ወስደው ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርገዋል የተባሉ ተከሳሾች በእስራት ተቀጡ፡፡

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሾቹ 1ኛ በረከት ብርሃኑ፣ 2ኛ ዮናስ ካሳ እና 3ኛ ዳግም ውብሸት ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት በማሰብ መስከረም 6 ቀን 2012 ዓ.ም በግምት ከጠዋቱ 12፡30 ሰዓት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ሰላም ፍሬ ጤና ጣቢያ አካባቢ በባጃጅ በመጓዝ ላይ ሳሉ መንገድ ዳር ቆማ ታክሲ በመጠበቅ ላይ የነበረችውን ወ/ሮ እጸገነት አንተነህ የተባለች ግለሰብ ትሄጃለሽ ብለው በመጠየቅ አሳፍረው ውስጥ ለውስጥ በኮብል ስቶን መንገድ መውሰዳቸው ተጠቅሷል፡፡

በአካባቢው ሰው አለመኖሩን ካረጋገጡ በኋላም በወቅቱ የያዘችውን ንብረት ለመውሰድ እንዲያመቻቸው 3ኛ ተከሳሽ አንገቷን በእጁ አንቆ ሲይዛት፣ 2ኛ ተከሳሽ እግሯን በመያዝ ስልክ፣ ቦርሳ፣ ጃኬቶች እና ሱሪዎች፣ የብር የአንገት ሀብልና የጣት ቀለበት ከወሰዱባት በኋላ ከባጃጁ አውርደው መንገድ ላይ ጥለዋት መሰወራቸው በክሱ ዝርዝር ላይ ተመላክቷል፡፡

የወሰዱትን ንብረትም ሸጠው ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው በማዋል እና ግለሰቧም በእጅ አንገቷን በመታነቋ እና በራሷ ላይ በደረሰባት ጉዳት ምክንያት ሕይወቷ በዚሁ እለት እንዲያልፍ ያደረጉ በመሆኑ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ እና 671/2/ መሰረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀሙት ከባድ ውንብድና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ ሁሉም ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር አቅርበው ያሰሙ ቢሆንም የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ ሰጥቷል።

ከዚህ ቀደም ወንጀለኞቹ በ14 ዓመት ተቀጥተው የነበረ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ጠይቆበት በድጋሚ በተሻሻለ ውሳኔ መሰረት 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በ20 ዓመት፣ 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ በ16 ዓመት እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኗል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.