Fana: At a Speed of Life!

ክልሉን የሰላምና የልማት ተምሳሌት ማድረግ ይጠበቅብናል – አቶ ጥላሁን ከበደ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ክልሉን የሰላም፣ የልማትና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ፡፡

በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘዉ የደቡብ የክልሉ የመንግስት እና የፓርቲ ሥራዎች አፈፃፀም ግምገማ መድረክ እንደቀጠለ ነዉ።

በመድረኩ ርዕሰ-መስተዳድር ጥላሁን ከበደ÷ የመድረኩ ዓላማ በአመራሩ መካከል የተግባርና የአመለካከት አንድነት በመፍጠር በቀሪ ጊዜያት ለሕዝቡ የተገባውን ቃል ተፈፃሚ ማድረግ ነው ብለዋል።

ክልሉ ሲመሰረት የነበረዉ የሕዝብ ድጋፍ ትልቅ ዕድል የሰጠ እንደነበር አስታውሰው፤ የተደራጀ የሕዝብ ንቅናቄ በመፍጠር ፈጣን ምላሽ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

አመራሩ ክልሉን የሰላም፣ የልማትና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚጠበቅበት ጠቅሰው፤ ጠንካራ ፓርቲና መንግስት ለመገንባት የተያዘው ውጥን የደረሰበት ደረጃ እንደሚገመገም መግለፃቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በመድረኩ የፓርቲና መንግስት አቅምን የሚያጠናክሩ ቀጣይ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ይጠበቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.