Fana: At a Speed of Life!

የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት በ100 ሚሊየን ብር በጅግጅጋ ያስገነባው የዱቄት እና ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት በ100 ሚሊየን ብር ወጪ በጅግጅጋ ከተማ ያስገነባው የዱቄት እና ዳቦ ፋብሪካ በዛሬው ዕለት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ፡፡

በሥራ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ፣ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ፋብሪካው በቀን 300 ሺህ ዳቦና 420 ኩንታል ዱቄት የማምረት አቅም እንዳለው ተገልጿል፡፡

እስካሁንም በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት አማካኝነት በአዲስ አበባ፣ አጋሮ፣ ጎንደር፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሐረር፣ ቦንጋ እና ሐዋሳ የዱቄትና ዳቦ ፋብሪካዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ዛሬ በጅግጅጋ የተመረቀው ፋብሪካ ስምንተኛ ሲሆን÷ በአዲስ አበባ ከተመረቀው ውጭ ሁሉም ተመሳሳይ የማምረት አቅም እንዳላቸውም ተጠቅሷል፡፡

በጽሕፈት ቤቱ አማካኝነት የሚገነቡት የዱቄትና የዳቦ ፋብሪካዎች በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወኑ ናቸው ተብሏል፡፡

ተጨማሪ ፋብሪካዎች በደሴ፣ ነቀምቴ፣ አሶሳና ሠመራ ከተሞች በግንባት ላይ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን÷ የደሴው በቅርቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት በተለያዩ ከተሞች 12 የዱቄት እና ዳቦ ፋብሪካዎችን ለመገንባት እየሠራ ሲሆን በጅግጅጋ የተገነባውን ጨምሮ ስምንት ፋብሪካዎችን ወደ አገልግሎት ገብተዋል፡፡

በፍሬሕይወት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.