Fana: At a Speed of Life!

የቀድሞ የአ/አ ከተማ ከንቲባ የፕሮቶኮል ዳይሬክተር እነ ኤልቤቴል ከ44 ሚሊየን ብር በላይ ግለሰቦችን በማታለል ከባድ የሙስና ክስ ቀረበባቸው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞ የአ/አ ከተማ ከንቲባ የፕሮቶኮል ዳይሬክተር እነ ኤልቤቴል ከ44 ሚሊየን ብር በላይ ግለሰቦችን በማታለል ከባድ የሙስና ክስ ቀረበባቸው።

ክስ ከተመሰረተባቸው 12 ተከሳሾች መካከል 1ኛ የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት የፕሮቶኮል ኃላፊ የነበረችው ኤልቤቴል ሃብቴ ፣2ኛ ፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዓ/ህግ ዘርፍ ሃብት አስተዳደር ዳይሬክተር ፍቅሩ ኦላኒ 3ኛ የአ/አ አሽከርካሪ ተሸከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ቂርቆስ ክ/ከተማ ጽ/ቤት የተሸከርካሪ መረጃ አጠናካሪ ባለሙያ ዘሪሁን ሞገስ እንዲሁም የዚሁ ተቋም የቴክኒክ ባለሙያ የሆኑት አላዩ ባሳዝን እና ቴዎድሮስ አበበ ይገኙበታል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል፣ ከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል እና በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ምንጩን ለመደበቅ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የሚሉት ተደራራቢ ክሶችን አቅርቦባቸዋል።

ክሱ የተመሰረተባቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

በአንደኛው ክስ ላይ 1ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ፣ 5ኛ፣ 6ኛ፣ 10ኛ እና 12ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ በቀረበው ዝርዝር ክስ እንደተመላከተው 3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች የአሽከርከሪ ተሸከርካሪ ፍቃድ ቁጥጥር ባለስልጣን በ2010 ዓ.ም ያወጣውን መመሪያና አሰራር በመተላለፍ በሌላ ሰው ስም የተመዘገበ የተሽከርካሪ የሻንሲ ቁጥር በመቀየር ሊብሬ እና ሰሌዳ ቁጥር በህገ-ወጥ መንገድ 1ኛ፣ 6ኛ፣ 10ኛ እና 12ኛ ተከሳሾች እንዲወስዱ ማድረጋቸው በክሱ ተጠቅሷል።

1ኛ፣ 6ኛ፣ 10ኛ እና 12ኛ ተከሳሾች ደግሞ የሻንሲ ቁጥሩን ያስቀየሩትና ሊብሬና ታርጋ በህገወጥ መንገድ የወሰዱበትን ተሽከርካሪን ለ3ኛ ወገን በማስያዥያነት በመስጠት የማይገባቸውን 3 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ብልጽግና በማግኘት በግል ተበዳዮች ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ በዋና የሙስና ወንጀል አድራጊነት እና በልዩ ወንጀል ተካፋይነት በመሆን ስልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ ሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በሁለተኛው ክስ ደግሞ በ1ኛ፣ በ2ኛ፣ 6ኛ፣ 10ኛ እና 12ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ በቀረበው ክስ እንደተመላከተው የተጠቀሱት ተከሳሾች በግንቦት ወር 2014 ዓ.ም የግል ተበዳይ ከሆኑት ከ1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ጋር በመተዋወቅ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 01 ጀሞ ሚካኤል አካባቢ ካፌ ውስጥ ከግል ተበዳይ ጋር በመገናኘት 1ኛ ተከሳሽ ከንቲባ ጽ/ቤት የምትሰራ መሆኑን እና ” ቢ.ኢ.ኢ.ኤም ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር የተባለ ድርጅት በቤተሰብ አቋቁመን ከውጭ ሀገር እቃ እናስመጣለን ” በማለት የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችን ስም በመጥቀስ “ጨረታ ከነሱ ጋር እናመቻቻለን ፣ ወንድሜ እቃ ከውጭ እያመጣ አትራፊ ነው ከኛ ጋር ስሩ” በማለት አሳሳች የማግባቢያ አሳሳች ቃላት መጠቀሟ በክሱ ተገልጿል።

በተጨማሪም ተከሳሾቹ አሳሳች ፍሬ ነገር በመግለፅ የግል ተበዳይዎችን እምነት እንዲጨምር በማድረግ ከ1ኛ እስከ 4ኛ የተጠቀሱ የግል ተበዳይ የሆኑ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች አዳማ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ በሀዘን በመኖሪያ ቤታቸዉ ተቀምጠው እያለ 1ኛ ተከሳሽ ቤታቸው በመሄድ የጎማ ጨረታ ኤልሻዳይ የተባለ ድርጅት ለማቅረብ አሸንፈን ከፍተኛ ገንዘብ አስይዘን 14 ሚሊየን ብር የጎደለን ስለሆነ ያስያዝነዉን ከፍተኛ ገንዘብ ልንበላ ነዉ አብረን ስለምንሰራ ይሄንን የጎደለንን ገንዘብ ስጡን በማለት የጠየቀች መሆኑ በክሱ ተዘርዝሯል።

ለመተማመኛ በሚል ደግሞ የሰሌዳ ቁጥር አ.አ የሆነ ኮድ 02-B81421 ተሽከርካሪ ገዝተን 200 ሺህ ብር የቀረብንን ከፍለን የራሳችን የምናደርገዉ ነዉ በማለት የሌላ ግለሰቦችን ንብረት የራሳቸው ለማስመሰል 3 ተሽከርካሪዎችን ለግል ተበዳዮቹ ያቀረቡ መሆኑ በክሱ ተገልጿል።

በተጨማሪም 1ኛ፣ 2ኛ እና 12ኛ ተከሳሾች በ2015 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ የ3ኛ እና 4ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች መኖሪያ ቤት በመሄድ 4ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክርን ልጅሽን አምጪ ወይም አድራሻዉን ንገሪን እና ያስመታዉን ቼክ ያምጣ ያለበለዚያ ችግር ይደርስበታል በማለት በማስፈራራት ቤት በር ላይ መኪና ውስጥ ሆነዉ በተደጋጋሚ እየተመላላሱ ሌሊቱን ሙሉ በማስፈራራት ያደሩ መሆኑ በክሱ ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የግል ተበዳይ የሆኑትን ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተራ ቁጥር የተገለፁትን የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች የሆኑትን የግል ተበዳዮችን በማታለል፣ በማስፈራራት ጭምር የሌላ ሰው ንብረት የሆኑትን ተሸከርካሪዎች በማስያዝ በሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም አታለዉ ከግለሰቦቹ በተለያዩ መጠኖች አጠቃላይ 14 ሚሊዮን ብር ገንዘብ በመውሰድ በግል ተበዳዮች ላይ ጉዳት ያደረሱ መሆናቸዉ ተጠቅሶ በከባድ የአታላይነት የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።

በ3ኛ ክስ ደግሞ በ1ኛ፣ 2ኛ፣ ከ6ኛ እስከ 12ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱተሰ ተከሳሾች ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለራሳቸዉ ወይም ለሌላ ሰዉ ለማስገኘት በማሰብ የካቲት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ውስጥ ከ5ኛ እስከ 13ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱትን የግል ተበዳይ የሆኑ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን በተለያየ ቀን እና ቦታ በማግኘት 6ኛ ተከሳሽ የኬ.ኬ አስመጪና ንግድ ሥራ የተባለ ድርጅት ባለቤት ሆኖ ጀነሬተሮች፣ የህትመት እቃዎች፣ የኪችን እቃ፣ የመኪና ጎማ፣ የመኪና መለዋወጫ፣ ጌጣጌጦች ከውጭ ሀገር በማስመጣት ስራ እንደሚሰራ በሀሰት መናገሩ በክሱ ተጠቅሷል።

1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ደግሞ ከ6ኛ እስከ 12ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ጋር በመሆን የግል ተበዳይ የሆኑትን ግለሰቦችን የመኪና ጎማን ጨምሮ የተለያዩ እቃዎችን ከውጭ እናስመጣለን በማለት በማታለል ንግድ ፍቃድ በማሳየት፣ ያሳገዱትን እና ያዘጉትን የተለያዩ ቼኮችን ለመተማመኛ የሚል በመስጠት አታለዉ 30 ሚሊየን 689 ሺህ ብር የወሰዱ እና በግል ተበዳዮቹ መታለላቸውን አውቀው ገንዘባቸው ስጡን ብለው ሲጠይቁ ለውይይት በማለት በሆቴሎች በመጥራት ሲያስፈራሯቸው እንደነበር በክሱ የጠቀሰው ዐቃቤ ሕግ ከባድ የአታላይነት የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

በ 4ኛ ክስ ደግሞ በ1ኛ፣ 2ኛ፣ 6ኛ፣ 7ኛ፣ 9ኛ እና 10ኛ ተከሳሾች የቀረበ ሲሆን፣ ይኸውም ከግል ተበዳዮች በማታለል ያገኙትን 44 ሚሊዮን 689 ሺህ ብር በተለያዩ መጠኖች በተለያየ ግዜ ወጪ በማድረግ ለራሳቸዉ ጥቅም ያዋሉ በመሆኑ ምንጩ እንዳይታወቅ ወይም እንዲደበቅ ያደረጉ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብ ህጋዊ አድርጎ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ተከሳሾቹ ችሎት ቀርበው ክሱ የደረሳቸው ሲሆን የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለየካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.