Fana: At a Speed of Life!

የትኛውም መሬት ጾም እንዳያድር ለሚሰሩ የከተማዋ አርሶ አደሮች የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ድጋፍ ይደረጋል- ኢ/ር ታከለ ኡማ 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትኛውም መሬት ጾም እንዳያድር ለሚሰሩ የከተማዋ አርሶ አደሮች የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ድጋፍ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለፁ።

ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በዛሬው እለት ከአርሶ አደሮች ተወካዮች ጋር ዛሬ ምክክር አድርገዋል።

በምክክር መድረኩም አርሶ አደሮቹ ከዚህ ቀደም ለስራቸው ማነቆ ነበሩ ያሏቸውን የካሳ ክፍያ፣ ድጋፍና ትኩረት ማጣት ጉዳዮች አንስተዋል።

ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው፥ በኮቪድ 19 ተጽእኖ ምክንያት ሊገጥም የሚችለውን የምርት እጥረት ለመቋቋም እና የከተማ ግብርናው የሚጠበቅበትን እዲወጣ፤ የትኛውንም ባዶ መሬት ወደ ምርት ለማስገባት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

አርሶ አደሮቹ ያነሷቸው ችግሮች ወደፊት ለመፍታት እንደሚሰራ ቃል የገቡት ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፥ በደላሎች ተታለው መሬታቸውን እንዳይሸጡም መክረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ፈትያ መሀመድ፥ አርሶ አደሮቹ ያሉባቸውን ችግሮች በመለየት ለምርታማነታቸው ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

“ከዚህ ቀደም ለልማት ይፈለጋል በሚል በአነስተኛ ካሳ ተወስዶ መሬታችንን ሳንጠቀምበት ቆይተናል ያሉ አርሶ አደሮችም በዚህ ወሳኝ ግዜ ወደ ምርት እንድንገባ መደረጉ አስደስቶናል” ሲሉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

“ራሳችን ተጠቅመን ለከተማዋ ለመትረፍ እንሰራለን” ያሉት አርሶ አደሮቹ “መንግስት ትራክተር፣ የውሃ ፓምፕ፣ የምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ ድጋፍ ሊያድርግልን መሆኑ ይበልጥ ለስራው አጋዥ ይሆንልናል” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረው ትኩረት በጣም ዝቅተኛ እንደነበር ያነሱት አርሶ አደሮቹ፥ “ሁሉንም ክፍት ተብለው የተለዩ ቦታዎችን ወደ ልማት ለማስገባት እና ምርታማ ለማድረግም በቂ ዝግጅት እና ሞራል ወደስራ ለመስራት ተነሳስተናል” ብለወዋል።

በሀብታሙ ተክለስላሴ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.