Fana: At a Speed of Life!

ከህዝቡ ጋር በመስራት ለሀገሪቱ ብልፅግና እውን መሆን በቁርጠኝነት ይሰራል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከህዝቡ ጋር በመስራት ለሀገሪቱ ብልፅግና እውን መሆን በቁርጠኝነት ይሰራል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

“ሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሀሳብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡

ህዝባዊ ውይይቱን የመሩት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን ለተነሱ ሀሳቦች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም÷ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ የሰላምና የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ህዝቡም ሰላሙን ለማስጠበቅ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡

አቶ ሽመልስ አብዲሳ÷ ከአሶሳ አዲስ አበባ ድረስ ያለው መንገድ ከፀጥታ ችግር ነጻ እንዲሆንና የመንገድ መሠረተ ልማቱም በአዲስ መልክ እንዲሠራ መንግስት ዕቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው÷ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በአማራ ክልል በኩል የሚከሰቱ ግጭቶችና የመንገድ መዘጋት ችግሮች እንዲፈቱ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ኢስሀቅ አብዱልቃድር÷ የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የክልሉ መንግስት ከህዝቡ ጋር እየሠራ ነው ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

በህዝባዊ ውይይቱ ላይ የተሳተፉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማህበረሰብ ተወካዮች በሶስቱ ክልሎች ተጎራባች አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችና የመንገድ መሠረተ ልማት ችግሮች እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተለይ የሰላም እጦት፣ የመንገድ መዘጋት፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ችግር፣ እንዲሁም እነዚህ ችግሮች የወለዱት የኑሮ ውድነት በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና እያስከተለ መሆኑን ተሳታፊዎቹ ገልፀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.