Fana: At a Speed of Life!

44ኛው የአፍሪካ ሕብረት አስፈጻሚዎች መደበኛ ስብስባ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 44ኛው የአፍሪካ ሕብረት አስፈጻሚዎች ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ዛሬ ማለዳ ተጠናቋል።

ስብሰባው “ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ስርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣ የሕይወት ዘመን፣ ጥራትና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት“ በሚል የአፍሪካ ሕብረት ባዘጋጀው የ2024 መሪ ሀሳብ ሲካሄድ ቆይቷል።

ምክር ቤቱ ከጥር 6 እስከ 17 ቀን 2016 ዓ.ም 47ኛው የአፍሪካ ሕብረት ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ በተወያየባቸው አጀንዳዎች ላይ ምክክር አድርጓል።

ሌሊቱን በዘለቀው የምክር ቤቱ ስብሰባ የሕብረቱ ተቋማትና አደረጃጀቶች፣ በምክር ቤቱ ስር የሚገኙ ኮሚቴዎችና ንዑሳን ኮሚቴዎች እንዲሁም የአጀንዳ 2063 የ10 ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል።

ሰላምና ደህንነት፣ ንግድና ትስስር፣ ተቋማዊ ማሻሻያዎች፣ ትምህርት፣ ግብርናና የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሰብዓዊ መብቶች፣ ስርዓተ ጾታና ወጣቶችን ማብቃት እንዲሁም የተቋማትና አደረጃጀቶች ምርጫ ውይይት ከተደረገባቸው አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

ምክር ቤቱ የካቲት 9 እና 10 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚከናወነው 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችንም ማጽደቁን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.