Fana: At a Speed of Life!

በምስራቅ ጉጂ ዞን የሸኔ ሎጂስቲክስና የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ገመዳ ዱጎ እጅ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ጉጂ ዞን የኦነግ ሸኔ ሎጂስቲክስ እና የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ የነበረው ገመዳ ዱጎ ወይም በቅጽል ስሙ ሎንግ እጁን ሠጠ።

በምስራቅ ጉጂ እና አካባቢው ሲንቀሳቀስ በነበረው የሸኔ ቡድን ላይ ሠራዊቱ እየወሰደ በሚገኘው የተቀናጀ ወታደራዊ እርምጃ የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች እጃቸውን እየሰጡ እንደሚገኙ የክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ገብሬ ጋሞ ገልጸዋል።

ሰራዊቱ በሳባቦሩና ዳዋ በሚባሉ አካባቢዎች በጠላት ላይ በወሰደው እርምጃ ከፍተኛ ድል መቀዳጀቱን ነው የተናገሩት፡፡

የሰራዊቱን ብርቱ ክንድ መቋቋም ያቃተው የቡድኑ ታጣቂ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር በመቻሉ በምስራቅ ጉጂ ዞን የሸኔ ሎጂስቲክስ እና የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ የሆነው ገመዳ ዱጎ ወይም ሎንግ በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቀው የቡድኑ አመራር ለሰራዊቱ እጁን ሰጥቷል ብለዋል።

ሰራዊቱ አስቸጋሪና ፈታኝ በሆኑ መልክዓ ምድሮች ላይ ግዳጁን በብቃት ከመወጣቱም ባሻገር የቡድኑን እኩይ አላማ በመበጣጠስ እና ጠላትን እፎይታ በመንሳት ተገደው እጃቸውን እንዲሰጡ እየተደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

በጉጂ ዞን የሸኔ ሎጂስቲክስና የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ የነበረው ገመዳ ዱጎ ምንም ዓላማ በሌለው እና ሕዝብን በሚጎዳ ተግባር ላይ መሳተፉ ምንም ጥቅም የሌለው መሆኑን ተናግሯል፡፡

ያለምንም ትርጉም ሕዝብን መበደል እንደማያዋጣ በማመን ለሰራዊቱ እጁን እንደሰጠም ነው ያስረዳው፡፡

ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የሽብር ቡድኑን እንደተቀላቀለ የሚናገረው የቡድኑ ከፍተኛ አመራር ላለፉት በርካታ ዓመታት ህዝብን በማሰቃየትና በመዝረፍ ላይ የተሰማራው ሸኔ በሰራዊቱ በተወሰደበት እርምጃ እየተበታተነ እና አመራሩም ጭምር በሃሳብ እየተፈረካከሰ እንደሚገኝ አብራርቷል።

ቡድኑ አሁን ላይ ህዝብን ከመዝረፍ ውጪ ምንም ዓላማ ስለሌለው እጁን እንደሰጠ መጥቀሱንም የመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡

በየጫካው ተበታትነው የሚገኙ ርዝራዥ የቡድኑ ታጣቂዎች ለሰራዊቱ እጃቸውን በመስጠት ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው ሊመለሱ እንደሚገባም ጥሪ አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.