Fana: At a Speed of Life!

የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ሊያደርጓቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የስኳር ህመም የሚከሰተው ሰውነታችን ኢንሱሊን የተባለውን ንጥር ነገር በበቂ ሁኔታ ማምረት ሲያቅተው ወይንም የተመረተው ኢንሱሊን ስራዉን በአግባቡ መስራት ሳይችል ሲቀር ነው፡፡

የስኳር ህመም አንድ ጊዜ ከተከሰተ ወይም ከመጣ በኋላ በዋናነት የህክምናው ግብ የስኳር መጠንን መቀነስና ሌሎች ተዛማጅ በሽታዎችን (ደም ግፊት፣ ኮሊስትሮል፣…) መቆጣጠር ይሆናል።

አንድ ታካሚ የስኳር መጠኑን ለመቀነስ ከሃኪሙ ጋር በመነጋገር “ስኳሩ ከዚህ በላይ እንዳይሆን” በሚል ግብ ያስቀምጣሉ።

በዚህም ታካሚዎች ከሃኪማቸው ጋር በመነጋገርና በመመካከር ጥሩ የስኳር ቁጥጥር ሊኖራቸው ይገባል።

ይህንን ለማድረግ በዋናነት አመጋገብ ላይ መሥራት ያስፈልጋል፤ በመሆኑም የስኳር መጠንን የማይጨምሩ ምግቦችን መውሰድ፣ በተቃራኒው ደግሞ የፋብሪካና ጣፋጭ የሆኑ ምግቦችንና ምርቶችን ከገበታችን ማውጣት ያስፈልጋል።

አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጤናማ ፕሮቲኖችንና የቅባት ምግቦችን አካቶና አመጣጥኖ መመገብ አንዱ የህክምና መንገድ ነው።

ሁለተኛው የህክምና መንገድ ደግሞ አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ሲሆን÷ አንድ የስኳር ታካሚ በሳምንት 150 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሊያደርግ ይገባል።

ነገር ግን በተለይ የእግር የደም ቧንቧ መጥበብ፣ እግሩ ላይ ቁስል ያለበት እንዲሁም ደግሞ የልብ ችግር ያለበት ሰው ከሃኪም ጋር ሳይመካከር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ፈጽሞ ማድረግ የለበትም።

ስለዚህ የስኳር ታካሚዎች በህክምና ተቋም ውስጥ ከሃኪሞቻቸው ጋር አዘውትረው ክትትል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ሌላኛው በሃኪሞች የሚታዘዙ መድሃኒቶችን በታዘዘው መሰረት በአግባቡ ሰዓቱን ሳያዛቡ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ከአዲስ አበባ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ሌላው ነገር ቤት ውስጥም ቢሆን አልፎ አልፎ የስኳር መጠንን መለካትና መከታታል ይኖርባቸዋል፤ ከዚህ በተጨማሪ በስኳር አማካኝነት የሚመጡ ተዛማጅ ህመሞች እንዳይከሰቱ ቀድሞ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።

አንድ ታካሚ ከላይ የተጠቀሱ የስኳር ህመምተኞች ሊያደርጓቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎችን ካደረገ ጥሩ ጤንነትና የተሻለ የስኳር ቁጥጥር እንደሚኖረው የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.