Fana: At a Speed of Life!

አባቶቻችን ያስረከቡንን የአፊኒ ሥርዓት የአሁኑ ትውልድ የበለጠ ማጎልበት ይጠበቅበታል – አቶ ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አባቶቻችን በትጋት ጠብቀው ያስረከቡንን የአፊኒ ሥርዓት የአሁኑ ትውልድ በይበልጥ በማጎልበት ግዴታውን እንዲወጣ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ አሳሰቡ፡፡

የሲዳማን ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓት የሚያሳይ አፊኒ ፊልም በሐዋሳ ከተማ ተመርቆ ለዕይታ በቅቷል፡፡

ርዕሰ መሥተዳድር ደስታ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ አፊኒ በሲዳማ ሕዝብ ውስጥ የፍትሕ ሥርዓትን ያሰፈነ  የግጭት አፈታት ዘዴ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሲዳማ ክልል እራሱን ማሥተዳደር ከጀመረ ወዲህ ከተገኘው ትልቅ ዕድል አንዱ አፊኒ ፊልም ለዚህ መብቃቱ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የቀደሙ አባቶቻችን ከማይዳሰስ ቅርስ ውስጥ አንዱ የሆነውን አፊኒ ሥርዓትን ያለምንም መበገር ለዛሬ አድርሰዋልና የአሁኑ ትውልድም ሥርዓቱን የበለጠ ማጎልበት ይገባዋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ጃጎ አገኘሁ በበኩላቸው÷ አፊኒ ፊልም የተሠራው የሲዳማን ባህል ለትውልድ ከማስተላለፍ ባሻገር ከሀገር አልፎ ለዓለም ቅርስ እንዲሆን ለማድረግ  መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የሲዳማ ሕዝብ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ የሆነው አፈኒ ሥርዓት እውነትን በመፈለግ ፍትሕ ላይ የተመሰረተ ዕርቅ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

በደብሪቱ በዛብህ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.