Fana: At a Speed of Life!

የታንዛንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ መታሰቢያ ሐውልት ቆመላቸው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የነጻነት ታጋዩና የታንዛንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ በአፍሪካ ሕብረት ቅጥር ግቢ የመታሰቢያ ሐውልት ቆመላቸው።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት፣ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር መሐመድ ኦውልድ ጋዙዋኒ፣ የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን እንዲሁም የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የቀጣናዊ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

“የታንዛንያ አባት” እየተባሉ የሚጠሩት ጁሊየስ ኔሬሬ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ በነበረው ትግል ውስጥ ስማቸው በቀዳሚነት ከሚነሱ ሰዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

ታንዛንያ (በወቅቱ ታንጋኒካ) ከብሪታኒያ ቅኝ ግዛት እንድትወጣ ታንጋኒካ አፍሪካን ዩኒየን የተሰኘ ፓርቲ በማቋቋም ትግል አድርገዋል።

ትግሉም ፍሬ አፍርቶ በፈረንጆቹ 1961 ታንዛንያ ከቅኝ ግዛት የወጣች ሲሆን ኔሬሬም በ1964 የመጀመሪያው የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ሆኑ።

ኔሬሬ እስከ ፈረንጆቹ 1985 የሀገሪቷ ፕሬዚዳንት በመሆን ማገልገላቸውን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

መምህር (ሙዋሊሙ) የሚል ቅጽል ስም ያላቸው ኔሬሬ የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ ነበሩ።

ጁሊየስ ኔሬሬ “ያለ አንድነት አፍሪካ ምንም መጻኢ እድል የላትም” በሚለው ታዋቂ አባባላቸው ይታወቃሉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.