Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከሞሮኮ እና አልጄሪያ ጋር በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመሥራት ተስማማች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከሞሮኮ እና አልጄሪያ ጋር በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመሥራት መግባባት ላይ መድረሷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከሞሮኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናስር ቡርታ ጋር ባደረጉት ውይይት÷ በግብርና እና በግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፎች በትብብር ለመሥራት ተስማምተዋል ፡፡

በተመሳሳይ አምባሳደር ታዬ ከአልጄሪያ አቻቸው አሕመድ አታፍ ጋር ባደረጉት ውይይት÷ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን መድረኮች ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባዎችን በቀጣይ ለማካሄድም መግባባት ላይ ተደርሷል።

ከውይይቱ በኋላም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ÷ ከ37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቅ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራ እያከናወነች መሆኗን ገልፀዋል።

ከጉባዔው ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ነው ቃል አቀባዩ ያነሱት፡፡

በተጨማሪም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኩል ከተለያዩ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮችና ሚኒስትር ዴዔታዎች ጋር ፍሬያማ ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.