Fana: At a Speed of Life!

የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየጨመረ በመሆኑ የለይቶ ማቆያ ቦታዎችን ማስፋፋትና ማጠናከር እንደሚያፈልግ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየጨመረ በመሆኑ የለይቶ ማቆያ ቦታዎችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ማስፋፋት እና ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለፀ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በተለይም ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚዋሰኑባቸው ሰፊ ቦታዎች ያሏቸው ክልሎች ማእከላቱን ማስፋት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ከሰሞኑም ኢንስቲትዩቱ ከጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች አካላት ጋር ባደረገው ሀገር አቀፍ ቅኝት ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች ላይ ማእከላቱን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።

ከጎረቤት ሀገራት ጋር በስፋት የሚገናኙ ድንበሮች ያሏቸው እንደ አማራ፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ እና የመሳሰሉ  ክልሎችም የለይቶ ማቆያ ማእከላትን ማስፋት እና ማጠናከር እንደሚገባቸው ነው ዶክተር ኤባ ያነሱት።

ዶክተር ኤባ አባተ አክለውም፥ በለይቶ ማቆያ ማእከላት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በመንግስት የተቀመጡ ደንቦችን ማክበር ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ይናገራሉ።

ከውጭ ሀገር የሚመጡ እና በራሳቸው ወጭ በሆቴሎች ኳራንቲን የሚገቡት ላይ ብዙ ክፍተቶች ባይታዩም፤ በአስገዳጅ ሁኔታ ከውጭ ሀገር በተለይም ከጎረቤት ሀገራት የሚመጡ ሰዎች የሚገቡባቸው ማእከላት ላይ ህግን ያለማክበር እና ደንቦችን የመተላለፍ ነገሮች እንደሚስተዋሉ ዶክተር ኤባ ይናገራሉ።

ከውጭ ሀገራት በድንበር በኩል የሚመጡ እና በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የተደረጉ ኢትዮጵያውያኖች በማእከላት ውስጥ ለመቆየት አለመፈለግ፣ ከማእከሉ ለማምለጥ መሞከር እና ከሌላው ሰው ጋር በቅርብ ንክኪ የማድረግ ችግሮች ጎልተው እንደሚታባቸው ነው ዋና ዳይሬክተሩ የነገሩን።

ለዚህ ደግሞ ወደ ማእከላቱ ከመግባታቸው በፊት የስነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ ቢችሉ እነዚህን ደንቦች አይጥሱም ነበር የሚሉት ዶክተር ኤባ፥ ከገቡ በኋላም አምልጠው አንዳይወጡ እና መሰል የተቀመጡ ደንቦችን እንዲያከብሩ ራሳቸው ላይ ጫና እንዳይፈጥሩ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የስነ ልቦና ባለሙያዎችን አሰማርቷል ብለዋል።

እስካሁን 40 ባለሙያዎች በማእከላቱ ቋሚ የስነልቦና ድጋፍ መስጠት መጀመራቸውን የነገሩን ዶክተር ኤባ ይህም በሰዎቹ ላይ የሚታዩ መጨናነቆችን ለመቅረፍ እና የቫይረሱን ስርጭ የሚያስፋፉ ተግባራትን ለመከላከል ያስችላል ተብሎ እንደታመነበት ያብራራሉ።

በማእከላቱ ከስነልቦና ችግር ውጭ እንደ ማምለጥ ያሉ ክስተቶችን  በፀጥታ አካላት የመቆጣጠር ስራዎች ላይ በጥብቅ ክትትል እየተከወኑ መሆኑን በመግለፅ፤ ክፍተት ያለባቸው የሆቴል ኳራንቲኖች ላይም ቢሆን እርምጃ እየተወሰደባቸው ነው ብለዋል።

ከውጭ የሚመጡትም ብቻ ሳይሆን በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ኖሯቸው እና ተጠርጥረው ወደ ማቆያ የገቡት ላይ ችግሮች ጎልተው እንደሚታዩ እና ጠበቅ ያለ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ከማስመዝገብ በተጨማሪ ሰሞኑን በተከታታይ ቀናት በቫይረሱ ምክንያት ውድ ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎችንም እያስመዘገበች ነው።

ይህ ማለት ደግሞ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ የሚሄድ መሆኑን የሚያሳይ ነው የሚሉት ዶክተር ኤባ፥ ህብረተሰቡ ያለውን መዘናጋት ቆም ብሎ ማየት እና አሁን የዜግነት ግዴታውን መወጣት ያለበት ሰአት ላይ መድረሱን ማወቅ ይገባዋል ብለዋል።

ጥንቃቄ ባለማድረግ የምናጣው የሰዎች ውድ ህይዎትም ለነገው ትውልድ ጠባሳ ታሪክ ሆኖ የሚመዘገብ መሆኑንም ማጤን ይገባልም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።

በዙፋን ካሳሁን

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.