Fana: At a Speed of Life!

የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት መሆኑ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

ጉባኤውን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፥ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የእንግዶች ቆይታ ያማረ እንዲሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

በሶማሊያ መንግስት በኩል የቀረበው ውንጀላ ኢትዮጵያ ለእንግዶች ያደረገችውን እንክብካቤ የማይመጥን ነው ብለዋል።

ሁሉም መሪዎች ያለ ልዩነት አቀባበልና መስተንግዶ እንደተደረገላቸውም ጠቁመው፥ ኢትዮጵያ እንደ አስተናጋጅ ሀገር ሙሉ ኃላፊነት ወስዳ መስራቷን ገልጸዋል።

የጦር መሳሪያ ይዞ ወደ ጉባኤው ለመግባት መሞከር፣ ትኩረት ለመሳብና ያልተገባ ወቀሳ ለመሰንዘር ባለመ መልኩ ክስ መቅረቡ አስገራሚ እንደነበረ አብራርተዋል።

ችግሩ በህብረቱ የጸጥታ አካላት ብስለት መፈታቱን ተናግረዋል።

ጉባኤውን ለማስተናገድ ከተደረገው ቅድመ ዝግጅት ጀምሮ የተሳካ ስራ መሰራቱን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ በጉባኤው ዋና ዋና ስኬቶችን ማንጸባረቅ ተችሏል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በትምህርት መስክ ያስመዘገበችውን ስኬት መግለጻቸውን አስታውሰዋል።

የቀዳማዊት እመቤቶች መድረክ ላይም ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ሴቶችን ያማከለ የትምህርት ስርዓት ለሀገር እድገት ያለውን ሚና በስፋት ማንጸባረቃቸውን አብራርተዋል።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚዬም በእንግዶቹ መጎብኘቱና ከጉባኤው ጎን ለጎን ኢትዮጵያ በቀረጸቻቸው አጀንዳዎች መድረኮች መከናወናቸው ትላልቅ ስኬት መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።

ከበርካታ ሀገራትና ተቋማት ጋር የተደረጉ የሁለትዮሽ ውይይቶችም በጉባኤው የተገኘ ስኬት እንደነበረ በመግለጫው አንስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.