Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ከነበረው የመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ በተደረገ ኦፕሬሽን ከ210 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለረጅም ጊዜ በድብቅ ሲፈፀም ከነበረው የመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ ባለፉት ቀናት በተደረገ ኦፕሬሽን ከ210 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ዳንኤል አሰፋ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ በኦፕሬሽኑ በህገወጥ መንገድ የተወሰደ የህዝብ እና የመንግስት ገንዘብ ወደ መንግስት ካዝና እንዲመለስ ተደርጓል።

በብዙ ሰው ስም በመደራጀት እና በተለያየ ዓይነት ማጭበርበር የተወሰደ ከ376 ሺህ በላይ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ማዳን ተችሏልም ብለዋል የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ።

ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተገናኘም ታራሚዎች ላይ ያልተገባ አያያዝ ያደረጉ ከ30 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ነው የገለጹት።

በክልሉ ህግን ለማስከበርና  ፍትህ ለማስፈን ጥብቅ ክትትል ማድረጋችንን እንቀጥላለን ያሉት አቶ ዳንኤል፥ ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው ሪፖርት የተፈጠሩ ክስተቶችን ሙሉ ስዕል የያዘ አይደለም ብለዋል።

ሪፖርቱ ምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች ላይ ብቻ ያተኮረና የአመጽ ክስተቶች በነበሩበት ጊዜ የተወሰዱ እርምጃዎች ከግምት ያላስገባ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በአክሱማዊት ገብረህይወት

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.