Fana: At a Speed of Life!

የዘመናዊውን ቅኝ ግዛት ስርአት የሚቃወሙ ሀገራት ፎረም ምስረታ ስብሰባ ተካሄደ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሩሲያው ገዥ ፓርቲ “ዩናይትድ ራሺያ ፓርቲ” አዘጋጅነት የዘመናዊውን ቅኝ ግዛት ስርአት የሚቃወሙ ሀገራት ፎረም ምስረታ ስብሰባ ከፈረንጆቹ የካቲት 15 እስከ 17 ቀን 2024 በሞስኮ ከተማ ተካሂዷል።

መርሀ ግብሩ ላይ በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በኩል በተላለፈ መልእክት፤ ኢትዮጵያ ዘመናዊው የባርነት ስልት የሀገራትን ሁለንተናዊ የሉአላዊነት ህልውና ስለሚፃረር ሁሉም በጋራ ሊቆም እንደሚገባ አቋሟን አንፀባርቃለች።

ከጣልቃ ገብነት እና ከእጅ አዙር ግዞት ተላቆ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ ተገቢ እንደሆነ እና ይህም በተሟላ ደረጃ እውን ይሆን ዘንድ ሀገራት እጅ ለእጅ ተያይዘው ትግል ማድረግ እንዳለባቸው ተገልጿል።

በተለይም አፍሪካ እና በውስጧ ላሉ ሀገራት በቅኝ ግዛት እና በዘመናዊው ቅኝ ግዛት የደረሰባቸውን ያልሻረ ቁስል ለማከም እንዲቻል የዘመናዊ አለም ቅኝ ግዛት ስልትን በትብብር ማምከን እንደሚገባ አቶ አደም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ቀደምትና በቅኝ ያልተገዛች ሀገር መሆኗ ብሎም አፍሪካውያን ለነፃነት እና ለሉአላዊነት ባደረጉት ትግል እንደ ምሳሌ ስለሚያዩዋት በዚህ ረገድ ያለባት ሀላፊነት ከፍተኛ እንደሆነ አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ፈር ቀዳጅነት ከአፍሪካ ላይ የተገረሰሰው የቅኝ ገዢነት ትርክት አሁን ላይ መልኩን ቀይሮ እንደመጣና በሉአላዊ ሀገራት ላይ መጥፎ ጥላ በማጥላት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገትን እንዳያስመዘግቡ ማነቆ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በአፍሪካ ሀገራት ላይ የኢኮኖሚ ጫናዎችን በመፍጠር፣ ፖለቲካዊ ውጥረቶችን በማባባስ፣ የባህል ወረራን በማካሄድ፣ የሀይል ሚዛንን በማሳት ላይ መጠመዳቸውንና ይህንንም እኩይ አላማ ለማስፈፀም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትንና የረድኤት ድርጅቶችን በመሳሪያነት እንደሚጠቀሙ አብራርተዋል።

ይህም በቀድሞ ታሪካቸው ቅኝ ገዢ የነበሩበትን ለምድ ቀይረው በእጅ አዙር ሀገራትን ተገዢ ለማድረግ የሚሞክሩበት አካሄድ መሆኑ ልብ ማለት እንደሚገባና በተዘዋዋሪ ፍላጎታቸውን እየጫኑ እንደሆነ ማስተዋል ተገቢ መሆኑን ነው ያነሱት።

ይህ በመሆኑም ጠንካራ ትብብርና ህብረት መገንባት እንደሚያስፈልግና በሁለንተናዊ መልኩ ነፃነትን ለመቀዳጀት የሚደረገውን ትግል ሀገራት በጋራ መደገፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ኢትዮጵያም በብልፅግና ፓርቲ መሪነት ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ እየተጋች እንደምትገኝና በትብብር፣ በመደጋገፍ እና በሰጥቶ መቀበል መርህ የዜጎቿን ህይወት ለመቀየር እየጣረች እንደሆነ አብራርተዋል።

የእድገት ጉዞውም ከየትኛውም ሀይል አሉታዊ ጣልቃ ገብነት በፀዳ መልኩ ለማቀጣጠል መነሳቷን አቶ አደም አስረድተዋል።

ይህም በሁሉም ሀገራት ተግባራዊ ይሆን ዘንድ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ሀገራችን ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን እየተጫወተች እንደምትቀጥል ገልጸው፤ ሁሉም ሀገራት ከጎኗ መሰለፍ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.