Fana: At a Speed of Life!

የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመቆጣጠር አስገዳጅ መመሪያ በት/ቤቶች ተግባራዊ ሊደረግ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመቆጣጠር አስገዳጅ መመሪያ በትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት መሪ ስራ አስፈጻሚ ፈቃዱ ያደታ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ኤችአይቪ/ኤድስ በሀገር አቀፍ ደረጃ የስርጭት መጠኑ ከ1 በመቶ በታች ነው።

ሆኖም በተለያዩ ክልሎች ያለው ስርጭት እንደሚለያይ ገልጸው፥ በተለይም በጋምቤላ 4 ነጥብ 5፣ በአዲስ አበባ 3 ነጥብ 4፣ በሐረሪ እና በድሬዳዋ ደግሞ 3 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደሀገር ስርጭቱ ዝቅ ያለ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች ስርጭቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም በወጣት ሴቶች፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣ የአደንዛዥ እጽ ተጠቃሚዎች፣ ረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ የህግ ታራሚዎችና በጎዳና ላይ ንግድ የሚተዳደሩ ሴቶች በይበልጥ ለቫይረሱ ተጋላጭ እንደሆኑም ነው የጠቆሙት፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ አዲስ የመያዝ ምጣኔም ሆነ በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም በተለይ በወጣቶች ላይ የመያዝ ምጣኔው እንደታሰበው እየቀነሰ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ በወጣቶች ላይ የሚታየው ልቅ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት፣ በአንድ አለመወሰን እና ኮንዶም አለመጠቀም እንዲሁም አደንዛዥ እጽ መውሰድ ለቫይረሱ መስፋፋት ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውንም ነው ያነሱት፡፡

እንደከዚህ ቀደም የኮንዶም ስርጭት መቀዛቀዝና ዋጋውም ጭማሪ ማሳየቱ የቫይረሱን ስርጭት እንሚያፋጥነው ጠቅሰው፤ ይህን በመገንዘብ 55 ሚሊየን የኮንዶም ፓኬት ለክልሎች መሰራጨቱንና በቅርቡ ወደሀገር የሚገባ እንዳለም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ቫይረሱን ለመቆጣጠር በትምህርት ቤቶች ላይ በትኩረት ለመስራት አስገዳጅ መመሪያ ለመተግበር ጤና ሚኒስቴር ጥረት እያደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ይህም ስለኤችአይቪ ግንዛቤ ለመፍጠር እንዲሁም ሌሎች የመከላከል እና የመቆጣጠር ዘዴዎችን ትኩረት ሰጥቶ ለመተግበር ወሳኝ እንደሚሆንም አንስተዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ቫይረሱ በደማቸው ይገኛል ተብሎ የሚታሰበው 610 ሺህ 350 ሰዎች ሲሆኑ፥ ከእነዚህ መካከል ከ520 ሺህ በላይ ሰዎች ተመርምረው ራሳቸውን ያወቁ ሲሆን፤ በዚህም ቫይረሱ ይገኝባቸዋል ተብለው ከሚታሰቡት ውስጥ 84 በመቶ ራሳቸውን ተመርምረው አውቀዋል፡፡

ከእነዚህ መካከልም ወደ 96 በመቶዎቹ የጸረ-ኤችአይቪ መድሃኒት እንደሚወስዱ አቶ ፍቃዱ ገልጸው፤ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አንዱ መፍትሄ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የጸረ-ኤችአይቪ መድሃኒትን በአግባቡ እንዲወስዱ ማድረግና ማስተማር እንደሆነም አስረድተዋል።

በመሰረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.