Fana: At a Speed of Life!

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተደበቀ የእጅ ቦምብ የቤት እድሳት ሲካሄድ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕንጻ ተቋራጩ ከደንበኛው የቤት ግድግዳ ውስጥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተደበቀ የእጅ ቦምብ ማግኘቱ ተሰማ፡፡

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከፈረንጆቹ 1939 እስከ 1945 ድረስ የዘለቀ ዓለም ከፍተኛ ጉዳት ያስተናገደችበት ግጭት እንደነበር ይታወሳል፡፡

በጊዜው ያደጉ ሀገራትን ጨምሮ ብዙ የዓለም ሀገራት አሊያንስ እና አክሲስ በሚል ስያሜ የሁለት ተቃራኒ ወታደራዊ ጥምረት አካል በመሆን ተዋግተዋል።

ሀገራቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ኢንዱስትሪያላዊና ሣይንሳዊ አቅሞቻቸውን ጦርነቱ ላይ ያፈሰሱ ሲሆን፥ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ ቦምቦችና በጊዜው የነበሩ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

በዚህም ጦርነት ከ70 እስከ 80 ሚሊየን የሚሆን የዓለም ህዝብ ያለቀ ሲሆን፥ ዓለም ካስተናገደችው አሰቃቂ እልቂት ግንባር ቀደም በመሆን የሚነሳ ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ፎክስ ኒውስ ባስነበበው መረጃ በአሜሪካ ሲያትል ግዛት የሕንጻ ተቋራጩ የደንበኛውን የመታጠቢያ ክፍል ግድግዳ ለማደስ ሲያፈርስ ከጀርባው የዚሁ ጦርነት አካል የሆነውን የእጅ ቦምብ ማግኘቱ ተሰምቷል፡፡

ቫዲም ካርካቪ የተባለው የሕንጻ ባለሙያ ‘’የእጅ ቦምቡን ሣየው በቶሎ ያሰብኩት ከስፍራው መራቅ ነው’’ ሲል በጊዜው የተሰማውን ድንጋጤ ተናግሯል፡፡

እንዳሰበው ወደኋላ በመሸሽ ጥቂት ካሰበ በኋላ ወደውስጥ በመዝለቅ ቦምቡ የነበረበትን ሁኔታ መቅረጹንም ነው የገለጸው፡፡

ይህን ካደረገ በኋላም የሲያትል ፖሊስ እና የፈንጂ አምካኞች ቡድን ወደ ቦታው ተጠርተው ስለሁኔታው ያጣሩ ሲሆን፥ መሳሪያው ሊፈነዳ የሚችል እንዳልሆነም ነው ያረጋገጡት፡፡

ፖሊስ አክሎም፥ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ተሳታፊዎች ከጦርነት ወደ ቤታቸው ሲመለሱ መሳሪያ ይዘው ይመጡ እንደነበር አንስቷል፡፡

ይህ ክስተትም ከዚህ ጋር የተያያዘና ያስቀመጠውም ሰው ረስቶት ሊሆን እንደሚችል ፖሊስ ያለውን ግምት ገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.