Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደት የመሪነቱን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ የመሪነቱን ሚና እየተወጣ መሆኑን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ አስታወቁ፡፡

ኩባንያው ተቋማት ውጤታማ እንዲሆኑ፣ አገልግሎታቸውን በፍጥነት ተደራሽ እንዲያደርጉና ምርታማነታቸው እንዲጨምር የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ከለውጡ በፊት 37 ሚሊየን የነበረው የኩባንያው ደንበኞች ቁጥር ለውጡን ተከትሎ በተከናወኑ ሥራዎች እና በየጊዜው በሚደረጉ ማሻሻያዎች በ2016 አጋማሽ 74 ነጥብ 6 ሚሊየን መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡

የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከዚህ ቀደም 17 ነጥብ 8 ሚሊየን እንደነበር ጠቅሰው÷ አሁን ላይ 36 ነጥብ 4 ሚሊየን መድረሱን አንስተዋል፡፡

መንግሥት ለዜጎች የሚሰጠውን አጠቃላይ አገልግሎት ዲጂታይዝ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ኢትዮ ቴሌኮም አስቻይ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራዎቹን በጥራት እየተወጣ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ቀደም ሲል 20 በመቶ የነበረው የስማርት ስልክ ተደራሽነት አሁን ላይ ወደ 46 በመቶ ማደጉንም ጠቁመዋል።

ለዕድገቱ መሰረት የሆነውን ቴክኖሎጂ በማዳረስ በኩል አሁን ላይ 340 የሚሆኑ ከተሞች የ4ኛው ትውልድ (4ጂ) አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የብሮድባንድ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥርም 688 ሺህ መድረሱን አመላክተዋል፡፡

በዚህም በርካታ ተቋማት ያለምንም የቴክኖሎጂ ውስንነት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሥራቸውን መከወን የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ነው ያሉት።

ኩባንያው ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ የመሪነቱን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.