Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም ለመቀየር ሕዝቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል አሁን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም ለመቀየር ሁሉም የክልሉ ሕዝብ የድርሻውን መወጣቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ፡፡

የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ÷ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ግጭቶች ሊቆሙ ይገባል ብሏል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡-

በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ አጥፊ ግጭቶች ሊቆሙ ይገባል!

ሰላም ለሁለንተናዊ ለውጥ ቁልፍ ሚና አለው። በክልላችን በተሟላ ደረጃ ሰላም መስፍኑ አማራጭ የሌለዉ የወል ሀሳብ ሊሆን ይገባል፡፡

ዘለቄታ ያለውን ሰላም ለመገንባትም ያጋጠሙ ዝንፈቶችን በዉይይት ማረም አስፈላጊ ነዉ። ይህ እዉን እንዲሆንም የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ ይሻል።

በክልላችን የተፈጠረዉን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት በማህበረሰቡ ውስጥ ግጭት መነሻ የሆኑ መልከዓ ብዙ ምክንያቶችን ለማወቅ አስፈላጊ ዉይይቶች ተደርገዋል፡፡ እየተደረጉም ነዉ። ከዚህ ባሻግር ተጨማሪ ግጭቶች እንዳይከሰቱ መከላከያ ይሆን ዘንድ ስልቶችን መበንደፍ የሀገር የመከላከያ ሰራዊት፣ የክልላችን አመራርና የጸጥታ ሀይል ሌት ተቀን ያለ እረፍት እየሰራ ይገኛል።

ይሁን እንጅ በክልላችን አንዳንድ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሰላም ሀይሎች አውዳሚ ረብሻ በመከተል በክልላችን ቀውስ እንዲከሰትና በህዝብ ሀብትና ንብረት ላይም ሊጠገን የማይችል ጉዳት አያደረሱ ይገኛሉ፡፡ ይህ በህዝብ ስም የሚነገድ የፖለቲካ ፍላጎታቸዉ በህዝባችን ዘንድ ከፍተኛ ምሬትና ሮሮ ፈጥሯል።

የዚህ አጥፊ ድርጊት መሪ ተዋናዮች በከፋ ድርጊታቸዉ ከህዝብ በመነጠላቸዉ ከጊዜ ወደጊዜ አቅማቸዉ ተዳክሞ ተራ ዉንብድና ላይ እንዲሰማሩ ሁነዋል። የነዚህ ጸረ-ሰላም ሀይሎች መንገድ መዝጋት፣ ስርቆት፣ ዜጎችን ማገት፣ ተቋማትን እና መሰረተ ልማትን ማዉደም መገለጫቸዉ ከሆነ ሰነባብቷል።

ይህ ድርጊት ያማረረዉ የክልላችን ህዝብም የሰላም መንገድ እንዲከፈትና መንግስት ህግ እንዲያስከብር በተፈጠሩ የህዝብ መድረኮች በተደጋጋሚ ሲያነሳ ቆይቷል። መንግስትም ለህዝብ ጥያቄ መልስ በመስጠት ለሰላም የዘረጋዉ እጁ ሳይታጠፍ ከህዝብ ጋር በጋራ በመሆን ህግ የማስከበር ተግባሩን እየሰራ ነዉ።

ለዚህም ሰላም ወዳዱ ህዝባችን ከመከላከያ ሰራዊታችን እና ከክልላችን የጸጥታ መዋቅር ጋር በጋራ በመሆን እየታገላቸዉ ይገኛል። በዉጤቱም አንጻራዊ ሰላም ተመዝግቧል። የክልላችን ህዝብ ለሰላም መረጋገጥ እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት ሊመሠገን የሚገባው ነው።

በመሆኑም እንደህዝብ ለጋራ ሰላማችን በጋራ በመቆም አሁን የተገኘዉን አንጻራዊ ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም ለመቀየር ሁሉም የክልላችን ህዝብ የድርሻዉን መወጣቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ

ባህርዳር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.