Fana: At a Speed of Life!

የትዳር አጋሩን የገደለው ግለሰብ በ21 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “ከሌላ ወንድ ጋር ግንኙነት አለሽ” በሚል በቅናት ተነሳስቶ የትዳር አጋሩን ሕይዎት ያጠፋው ግለሰብ በ21 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ፡፡

የቅጣት ውሳኔው የተላለፈበት ስሜነህ ግርማ በለጠ ሕዳር 25 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 2፡20 በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 አስኮ ሰፈረ ወርቅ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው የትዳር አጋሩ የሆነችውን ሟች ማህሌት ፍቃዱን በተለያየ የአካል ክፍሏ ላይ በስለት በመውጋት ሕይወቷ እንዲያልፍ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

የግድያ ወንጀሉ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶ በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ሕ/አ 539/1/ሀ መሰረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ መቆየቱም ተመላክቷል፡፡

በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶት ተከሳሽ የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርብ ቢፈቀድለትም ማቅረብ ባለመቻሉ እና በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት በ21 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.