Fana: At a Speed of Life!

የጋራ ግብረ ኃይሉ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን አስመልክቶ የማጠቃለያ ግምገማ አካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል 37ኛው የመሪዎች ጉባኤ እና 44ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤን አስመልክቶ የማጠቃለያ ግምገማ አካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በማጠቃለያ ግምገማው ላይ ÷37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ፣ 44ኛው የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ እና 28ኛው የቀዳማዊ እመቤቶች ጉባኤ በሰላምና በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ከታህሳስ ወር ጀምሮ የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ የተቀናጀ ልዩ ኦኘሬሽን በማካሄዳችን ቀላል የማይባሉ የወንጀሎችን መከላከልና መቆጣጠር ችለናል ያሉት ኮሚሽነር ጀነራሉ ይህም ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም መጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ለተገኘው ስኬት ዋናው መሠረት ህዝቡ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ በበኩላቸው÷ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በስኬት መጠናቀቅ የፀጥታና ደህንነት ተቋማቱ በትብብር የመስራት ውጤት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ÷”ከ8ሺህ በላይ እንግዶችን ተቀብለን ያለምንም የፀጥታ ችግር ማስተናገድ የቻልነው የፀጥታ አካላት የ24 ሰዓት አገልግሎት በመስጠታቸው ነው” ብለዋል፡፡

የሪፐብሊካን ጋርድ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ጀማል አብዱሮ ከድር በበኩላቸው÷ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ መሳካት የፀጥታና ደኅንነት አካላቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በቅንጅት በመስራታቸው የተገኘ ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.