Fana: At a Speed of Life!

የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ የቀድሞ የአማራ ልዩ ሃይል አባላት ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ የቀድሞ የአማራ ልዩ ሃይል አባላት ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ፡፡

በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው፣ የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌ/ጄ መሃመድ ተሰማ፣ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌ/ጄ ብርሃኑ በቀለና የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስየ ደጀን ተገኝተዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በምርቃት ስነ-ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ አባላቱ ህዝባዊነትን ተላብሰው ተልዕኳቸውን በብቃት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የአማራ ህዝብ ቀደም ሲል በወራሪ ኀይሎች አሁን ደግሞ በክልሉ ውስጥ ባለው ፅንፈኛ ቡድን እንዲሁም ከሀገር ውጭ ባሉ ግብረአበሮቻቸው እየተፈተነ ይገኛል ብለዋል።

የቡድኑን እኩይ አላማና ሴራ ለማክሸፍ መጠነ ሰፊ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስራ ተከናውኖ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

ኮሚሽነር ደስየ ደጀን በበኩላቸው÷ለአንድ ሀገር ልማትና እድገት መረጋገጥ አስተማማኝ የሰላም ሁኔታ እና የፀጥታ ሃይል የመኖር አስፈላጊነት የሚያጠራጥር አይደለም ብለዋል።

የፀጥታ ሃይል ለተሰጠው ተልዕኮና ሃላፊነት እንዲሁም ሕዝብን ለማገልገል እስከ ሕይወት መስዕዋትነት መክፈል ይጠበቃል፤ለዚህም ዝግጁ መሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡

ለስልጠናው መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና ማቅረባቸውንም የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.