Fana: At a Speed of Life!

ከሕገ-ወጥ የገንዘብ ምንዛሪና ክምችት ጋር በተያያዘ 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሕገ-ወጥ የገንዘብ ምንዛሪ እና ክምችት ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ባከናወነው ሥራ 23 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ከተጠርጣሪዎቹ በተጨማሪ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ መያዙንም ነው የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ያስታወቀው፡፡
የሀገርን ኢኮኖሚ ለማዳከም የሚፈፀሙ ወንጀሎችን መነሻ በማድረግ በተለይም ሕገ-ወጥ የውጪ ሀገራት ገንዘብ ምንዛሪ በሚከናወንባቸው ቦታዎች እና ገንዘብን ከብሔራዊ ባንክ መመሪያ ውጪ በመኖሪያ ቤታቸው በሚያከማቹ ግለሰቦች ላይ ጥናት ሲያደርግ መቆየቱንም ጠቅሷል፡፡
ጥናቱን እና የሕዝብ ጥቆማን መነሻ በማድረግም 3 ሚሊየን 24 ሺህ 180 ብር፣ 20 ሺህ ሪያል፣ 3ሺህ 758 የአሜሪካ ዶላር እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ ከብሐየራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር መያዙን አስታውቋል፡፡

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ጋንዲ ሆስፒታል አካባቢ፣ በወረዳ 2 ሸዋ ዳቦ እና መስቀል ፍላወር አካባቢ እንዲሁም ከሕገ-ወጥ የውጭ ሀገራት ገንዘብ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ በጥናቱ በተካተቱ አራት ንግድ ቤቶች ላይ በተደረገ ብርበራ 350 ሺህ ብር፣ 2 ሺህ 803 ዶላር እና 20 ሺህ ሪያል መያዙን ገልጿል፡፡

በተጨማሪም መስቀል ፍላወር አካባቢ በሚገኝ አንድ ፔንሲዮን ውስጥ ብርበራ ሲደረግ በወረቀት ተጠቅልሎ ለሽያጭ የተዘጋጀ አደንዛዥ ዕፅ መገኘቱን ጠቁሟል፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ እና በጥናት በተለዩ 15 ንግድ ቤቶች ላይ በተደረገ ብርበራ የተያዘው 1 ሚሊየን 305 ሺህ ብር እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ መሆኑን አብራርቷል፡፡

ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ባከናወነው ሥራ ከገንዘብ በተጨማሪ ሐሰተኛ ገንዘብ ለማዘጋጀት በብር መጠን ተቆርጠው የተቀመጡ ወረቀቶች፣ የነዋነት መታወቂያዎች፣ ፓስፖርቶች እና የተለያዩ የባንክ ሠነዶች አግኝቻለው ብሏል፡፡

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ቀራንዮ የሺ ደበሌ አካባቢ አንድ ግለሰብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያን በመተላለፍ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ እና ከተፈቀደው መጠን ባላይ ብር ስለማከማቸቱ በደረሰ ጥቆማ ባደረኩት ክትትል በቁጥጥር ስር ውሏል ነው ያለው፡፡

በፍርድ ቤት ትዕዛዝም በተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት በተከናወነ ብርበራ 955 ዶላር፣ 2 ሺህ 270 የኤርትራ ናቅፋ እና 300 ሺህ የኢትዮጵያ ብር መገኘቱን ጠቅሷል፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 መነን አደባባይ አካባቢ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በግለሰብ መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራ 1 ሚሊየን 69 ሺህ 180 ብር ተከማችቶ በመገኘቱ መያዙን ጠቁሟል፡፡

በ23ቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ያሳወቀው ፖሊስ÷ ሕገ-ወጥ ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እና ሕብረተሰቡም ጥቆማውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.