Fana: At a Speed of Life!

እርግዝና እና ደም ግፊት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በእርግዝና ወቅት ደም ግፊት አብዛኛዉን ጊዜ በእርግዝና ሁለተኛዉ አጋማሽ ማለትም ከ20 ሣምንት በኋላ እንደሚከሰት ይነገራል፡፡

በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ደም ግፊት መንስኤን በተለያየ ጊዜ ጥናቶች ቢደረጉም አንዳንድ ሴቶች ለምን በእርግዝና ወቅት ደም ግፊት እንደሚኖርባቸው በትክክል ወይም መንስኤውን ለይቶ ለማወቅ አልተቻለም፡፡

ሆኖም ግን ከዚህ በታች የተጠቀሱት ምክንያቶች ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡-

• እርግዝና የመጀመሪያቸዉ የሆነ፣
• ከዚህ በፊት በእርግዝና ጊዜ የደም ግፊት የታየባቸዉ ወይም በቤተሰብ ዉስጥ ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸዉ፣
• ከዚህ በፊት የደም ግፊት፣ የኩላሊት ወይም ሁለቱም በሽታ የነበረባቸዉ፣
• እድሜያቸዉ ከ40 አመት በላይ የሆኑ፣
• እርግዝናዉ መንታ ወይም ከዚያ በላይ ሲሆን፣
• እንደ ስኳር አይነት ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸዉ፣
• ከመጠን በላይ የሰዉነት ክብደት።

አንዲት ነፍሰጡር ደም ግፊት ቢኖርባት በልጇ ላይ ምን ሊያስከትል ይችላል?

• የልጁ ክብደት ከእርግዝና ጊዜ ጋር ሲታይ የቀነሰ ይሆናል፣
• የሽርት ውሃ መቀነስ፣
• በእትብት በኩል ለልጁ የሚደርሰዉ ደም መቀነስ፣
• እንዲሁም ጽንሱ በማህጸን ውስጥ እንዳለ ሊሞት ይችላል።

ምልክቶቹ፡- የበሽታዉ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ምንም አይነት ምልክት አይታይም፤ በምርመራ ጊዜ የግፊት መጨመር (≥140/110) እና ሽንት ዉስጥ ያለዉ ፕሮቲን መጨመር ይታያል፡፡

ህመሙ አደገኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ፡-

• ከባድ ራስ ምታት፣
• የእይታ ለዉጥ (የእይታ ብዥ ማለት፤ የእይታ መጋረድ)፣
• ትንፋሽ ማጠር፣
• በሆድ የላይኛዉ ክፍል ላይ ከባድ የሆነ የህመም ስሜት፣
• ከፍተኛ የደም ግፊት (≥160/110)
• የፊት እና የእጆች ማበጥ ያሳያል፡፡

በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊትን ለመከላከል ምን ይደረግ?

1. ሁሉም ነፍሰጡር የቅድመ ወሊድ ክትትል እንዲያደርጉ ማበረታታት፡- የደም ግፊቱ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ትንፋሽ ሲያጥራቸዉ፣ ሲያንቀጠቅጣቸዉ እና አዕምሮአቸዉን ሲያስታቸዉ ወደ ህክምና የሚሄዱ ነፍሰጡሮች በተደጋጋሚ ያጋጥማሉ፣

ይህ ከመከሰቱ በፊት እርዳታ ማግኘት እንድትችል የቅድመ ወሊድ ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ነዉ፡፡

2. ደም ግፊት ያለባት ለመጸነስ የምታስብ ሴት የጤና ባለሙያ በማማከር ህመሙ በጤናዋ ላይ ችግር አለመፍጠሩን ለማጣራት የቅድመ እርግዝና ምርመራ ማድረግ ይኖርባታል፣

3. ክብደቷ ከተገቢዉ በላይ ከሆነ ከእርግዝና በፊት ክብደት መቀነስ ይኖርባታል፣

4. የስኳር ህመም ያለባት ሴት ከማርገዟ በፊት ህመሟን በቁጥጥር ስር ማድረግ አለባት፣

5. የእርግዝና ደም ግፊት የተጋለጡ እናቶችን ለመለየትና የመከሰት እድሉን ለመቀነስ የቅድመ ወሊድ ክትትል በመጀመሪያ ሦስት ወር መጀመር እንደሚገባት ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.