Fana: At a Speed of Life!

የህጻናት የተመጣጠነ ምግብ ዕጥረትን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ወርልድ ቪዥን ኢንተርናሽናል የህጻናት የተመጣጠነ ምግብ ዕጥረት ችግርን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ የሶስት ዓመት ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።

“የሕፃናት ርሀብና ያልተመጣጠነ ምግብ ዕጥረት በቃ” በሚል መርህ በአፍሪካ 27 ሀገሮች የሚተገበረው ፕሮጀክቱ፤ በዋናነት ሕፃናት ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ ተገልጿል።

በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክንያቶች ወደ 342 ሚሊየን የሚጠጋ የአህጉሪቱ ሕዝብ የምግብ ዋስትናውን ማረጋገጥ እንዳልተቻለም ተመላክቷል።

በዚህም በአፍሪካ የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ከማያገኙት 278 ሚሊየን ዜጎች 55 ሚሊየን የሚጠጉት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት እንደሆኑ ተነግሯል።

ይህን አሳሳቢ ችግር ትርጉም ባለው መልኩ ለመቅረፍ ወርልድ ቪዥን ኢንተርናሽናል አህጉር አቀፍ ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ይፋ አድርጓል።

ለፕሮጀክቱ ትግበራም 1 ነጥብ 7 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መመደቡ ተገልጿል።

በፕሮጀክቱ ይፋ ማድረጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥታ በመስራት ላይ እንደምትገኝ አስገንዝበዋል።

መንግስት ሕፃናትን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች እያከናወነ እንደሆነ ገልጸው÷ በተለይ የተመጣጠነ የምግብ ዕጥረትን ለመቅረፍ የሰቆጣ ቃልኪዳንን ይፋ ማድረጉን አስታውሰዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የሌማት ትሩፋትም የተመጣጠነ ምግብ ዕጥረትን ለመፍታት ከሚተገበሩ መርሐ-ግብሮች መካከል የሚጠቀስ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሥራ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል ያሉት ሚኒስትሯ÷ ኢትዮጵያ በዘርፉ እያካሄደች ያለው ክንውን ከተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦች ጋር የተሰናሰሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በወንድሙ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.