Fana: At a Speed of Life!

“የአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከኮሮና መከላከል ጥንቃቄ ጋር ተጣጥሞ ይካሄዳል” – አቶ ንጉሱ ጥላሁን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ)”የአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ መርሃግብር ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከሚደረገው ጥንቃቄ ጋር ተጣጥሞ ይካሄዳል” ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን አስታወቁ።

የአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ መርሃግብር ነገ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሀዋሳ አካባቢ ታቦር ተራራ ላይ ይጀመራል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን መርሃ ግብሩን አስመለክተው ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ነገ የሚከበረውን የዓለም የአካባቢ ቀን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን በይፋ እንደምታስጀምር ገልጸዋል።

መርሃ ግብሩ በፌዴራል ደረጃ በሀዋሳ ቢጀመርም በሌሎች የአገሪቷ አካባቢዎች ችግኝ ተከላ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ሚጫ ወረዳ፣ በኦሮሚያ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወንጪ ወረዳ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን አንዱራ ወረዳና በጋምቤላ አኝዋክ ዞን በሚገኙ ወረዳዎችና በሌሎችም መርሃ ግብሩ ይካሄዳል ብለዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የወቅቱ ስጋት እንደሆነና በዚሁ ሳቢያ እንቅስቃሴ ተገድቦ ቫይረሱን የመከላከል ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ነው አቶ ንጉሱ ያስረዱት።

በወረርሽኙ ወቅት የምንከተለው መርህ “ምርት እናመርታለን ወረርሽኙን እንከላከላለን” የሚል በመሆኑ ወረርሽኙን እየመከትን የምርት ስራችንን እንቀጥላለን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.