Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የኑሮ ውድነትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንሱ ሥራዎች ላይ በትኩረት ይሰራል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስከ ወረዳ ካሉ አመራሮቻች ጋር ሲካሄድ የቆየው የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ተጠናቅቋል፡፡

በግምገማው ለሥራ እና ለኑሮ ምቹ የሆነች ከተማ ለመገንባት የተጀመሩ ሥራዎች ያሉበት ደረጃ መለየታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

ውጤት ከተገኘባቸው እና ካተሳኩ ሥራዎች ውስጥ የአመራር የሃሳብ እና የተግባር አንድነት በመገንባት አመራሩ ሥራ ላይ እንዲያተኩር መደረጉን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በተጨማሪ የከተማዋን ገጽታ ያሻሻሉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ከፍ የሚያደርጉ ትልልቅ እና ታሪካዊ ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ፣ በርካታ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖማዊ ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ እንዲሁም የሰው ተኮር ሥራዎች የከተማ ነዋሪዎችን ችግር ያቃለለ እንደሆነ መረጋገጡን ጠቅሰዋል፡፡

የበጎ ፈቃድ ሥራዎች እና የገቢ አሰባሰብ ሥራዎች አበረታች እንደሆኑ እና እነዚህም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተግባብተናል ብለዋል::

በቀጣይ ከህዝብ ችግር እና ጥያቄ አንፃር ለሕዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል በሰው ሃይል እና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተጀመሩ የማሻሻያ ሥራዎችን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ቅንጅታዊ አሰራርን በልህቀት መከወን፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ሁሉ ማጠናቀቅና የከተማዋን አጠቃላይ መሠረተ ልማት ማሻሻል፣ የኑሮ ውድነትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንሱ ስራዎች ላይ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ለወጣቶች ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር እንዲሁም ሌብነትና ብልሹ አሰራርን በማስወገድ ረገድ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.