Fana: At a Speed of Life!

ሕግ አስከባሪ በመምሰል በጦር መሳሪያ የመኪና ዘረፋ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቡድን ተደራጅተው ህግ አስከባሪ በመምሰል በጦር መሣሪያ በመታገዝ የመኪና ዘረፋ ወንጀል የፈፀሙ ወንጀለኞች እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ።

ተከሳሶቹ 1ኛ ለሙ ጊሼ፣ 2ኛ ወርቁ ጊሼ፣ 3ኛ በቀለ ያሚ፣ 4ኛ ኦላና ግርማ፣ 5ኛ አለማየሁ ሶሬቻ እና 6ኛ አወቀ ድረስ ይባላሉ፡፡

ተከሳሾቹ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በቡድን ተደራጅተው በጦር መሳሪያ የታገዘ የዘረፋ ወንጀል በአዳማ ከተማ አባ ገዳ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ አርባ ሜትር መንገድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሐምሌ 7 ቀን 2015 ዓ.ም ለፀጥታ ሥራ የሚጠቀሙበትን አንፀባራቂ ልብስ ለብሰው ሕግ አስከባሪ በመምሰል ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ ከተማ እየገቡ የነበሩ ሁለት አይሱዚ የጭነት ተሽከርካሪዎችን በማስቆም ሹፌሮቹንና ረዳቱን በሽጉጥና በጩቤ በማስፈራራት 80 ሺህ ብር እና የዕጅ ስልኮቻቸውን መቀማታቸው ተመላክቷል፡፡

በመቀጠልም አይናቸውን በማሰር በተለምዶ አሳማ ማርቢያ ተብሎ ወደ ሚጠራው ጫካ በመውሰድ እጅና እግራቸውን ከዛፍ ጋር በማሰር መኪናዎችን ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመውሰድ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እንደደበቋቸው የክስ መዝገቡ ያስረዳል።

መረጃው የደረሰው የአዳማ ፖሊስ ተጎጂዎችን ከታሰሩበት በማስፈታት መረጃ በማሰባሰብ ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጋር በጋራ ተከሳሾችን ከነ- ኢግዚቢቶቹ በቁጥጥር ሥር በማዋል ክስ እንዲመሰረትባቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አጠናቆ ለዐቃቤ ሕግ አቅርቧል።

ጉዳዩን የተመለከተው የአዳማ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዐቃቤ ሕግ የቀረበለትን ማስረጃ መርምሮ ህዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው የወንጀል ችሎት ተከሳሾቹን ያርማል፤ መሰል አጥፊዎችን ደግሞ ያስጠነቅቃል በማለት 1ኛ ተከሳሽ 25 ዓመት ከ2ኛ፣3ኛ፣4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ደግሞ እያንዳንዳቸው 24 ዓመትጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡

6ኛ ተከሳሽን ደግሞ 16 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣየተወሰነበት መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በሌላ መዝገብ 1ኛ በቀለ ያሚ፣ 2ኛ ለሙ ጊሼ፣ 3ኛ ወርቁ ጊሼ፣ 4ኛ አወቀ ደረሰ፣ 5ኛ ኦላና ግርማ፣ 6ኛ አሸናፊ ታደሰ፣ 7ኛ ዘካርያስ ቃሲም እና 8ኛ አብዱልከሪም ፈድሉ የተባሉ ወንጀለኞች በቡድን ተደራጅተው ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሰዓት ከአዳማ ከተማ ወደ አዲስ አበባ በቤት መኪና በመጓዝ ላይ የነበሩትን አቶ ንዋይ አበበን እና አቶ ግሩም ለገሰን በሽጉጥና በጩቤ በማስፈራራት አንድ ላፕቶፕ፣ ሶስት የሞባይል ስልኮችን እና አሥር ግራም ወርቅ የአንገት ሃብል መዝረፋቸው ተጠቅሷል፡፡

የአዳማ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ በማቅረብ የአዳማ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት 1ኛ ተከሳሽ 18 ዓመት በቀሪ 7ቱ ተከሳሾች ላይ ደግሞ እያንዳንዳቸው 16 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.