Fana: At a Speed of Life!

ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም (ልጅ ያሬድ) በተከሰሰባቸው የወንጀል ክስ ጥፋተኛ ተባለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም በቅጽል ስሙ ልጅ ያሬድ በተከሰሰባቸው የወንጀል ክስ ጥፋተኛ ተባለ።

የጥፋተኝነት ፍርዱን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ህገመንግስታዊና በህገመንግስት ስርዓቱ ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም ላይ ሶስት ክሶችን አቅርቦበት ነበር።

ከቀረቡበት ክሶች መካከል በኮምፒዩተር የሚፈጸም ወንጀል ድንጋጌን መተላለፍ፣ የቤተክርስቲያንና የሰዎችን ክብርና መልካም ስም ማጉደፍ እንዲሁም የጥላቻ ንግግር ማሰራጨት የሚሉ ተደራራቢ ክሶች ይገኙበታል።

ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም የቀረበበት ክስ እንዲሻሻል የክስ መቃወሚያውን በጽሁፍ ያቀረበ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ በኩል ክሱ ሊሻሻል የሚችልበት የህግ አግባብ እንደሌለ ተጠቅሶ መልስ ተሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን መርምሮ ተከሳሹ ያቀረበው የክስ መቃወሚያ ጥያቄ የህግ አግባብነት የለውም በማለት ውድቅ አድርጎታል።

ከዚህም በኋላ ተከሳሹ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን በመጥቀስ የዕምነት ክህደት ቃሉን በመስጠቱ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃውን አቅርቧል።

የቀረበውን ማስረጃ የመረመረው ችሎቱ ተከሳሹ የቀረቡበት ሶስት ክሶች ተጠቃለው በአዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀጽ 4 እና 7 መሰረት እንዲከላከል ብይን ተሰጥቷል።

ሶስቱም ክስ በአንድ እንዲጠቃለል የታዘዘው የወንጀል ድርጊቱ በሀሳብ፣ በጊዜና በቦታ ተመሳሳይ መሆኑን በምክንያትነት ተጠቅሶ ነበር።

ተከሳሹ የመከላከያ ማስረጃ አለኝ ማለቱን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ያቀረባቸውን የሰው መከላከያ ማስረጃዎችን ቃል አዳምጧል።

ተከሳሹ የሰው የመከላከያ ማስረጃ ያቀረበ ቢሆንም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል ባለመቻሉ እና በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት መፈጸሙ በፍርድ ቤቱ በመረጋገጡ በዛሬው ቀጠሮ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶበታል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት ለመጠባበቅ ለየካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዕምነት ተከታይ ምዕመናንን እና የማህበረሰቡን ክብርና ስነ-ልቦናን ከግምት ውስጥ በማስገባት የክሱ ዝርዝር ጉዳይ በሚዲያ እንዳይሰራጭ ትዕዛዝ መስጠቱን ተከትሎ ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ ተቆጥበናል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.