Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ለሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት ያልተቆጠበ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል – አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ለሀገራዊ ምክክር ሂደት ስኬታማነት የሚያደርገውን ያልተቆጠበ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ ተናገሩ።

የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው የመንግስት አስተዳደር ሥርዓቶች በአንድ በኩል በመልካም የሚጠቀሱ በሌላ በኩል መደገም የሌለባቸው ግድፈቶች አሉ።

በዚህም ቀጣይነት ላለው የሀገረ መንግስት ግንባታ አስተማሪ ሁነቶችን የጋራ ለማድረግ ግድፈቶችንም በሠላም፣ ዕርቅና ይቅርታ ለመዝጋት ቁጭ ብሎ መነጋገር ያስፈልጋል ብለዋል።

የአሁኑ ትውልድም ነገን የተሻለ ለማድረግ የራሱን ታሪክ በመፃፍ ብሔራዊ መግባባት ለሰፈነባት ኢትዮጵያ አሻራውን ማሳረፍ እንደሚኖርበትም ነው የተናገሩት።

በመንግስት ደረጃም የተለየ አቋም ያላቸው ሁሉ የጋራ አቋም የሚይዙበት መድረክ ለመፍጠር ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አቋቁሞ ወደ ስራ እንዲገባ ማድረጉን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በርካታ ሂደቶችን አልፎ በአሁኑ ወቅት ለምክክሩ ወሳኝ የሆኑ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑም ነው የተጠቆመው።

ለዚህም በተለያዩ አካባቢዎች የአጀንዳና ተሳታፊ ልየታ ተግባርን በፍጥነት በማጠናቀቅ በተያዘው ዓመት ወደ ዋናው የድርድርና የውይይት መድረክ ለመግባት ዕቅድ መያዙንም ነው ያነሱት።

መንግስት ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬታማነት የሚያደርገውን ያልተቆጠበ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጡት አቶ ተስፋዬ፥ ኢትዮጵያውያንም ለምክክሩ ውጤታማነት ሚናቸውን እንዲወጡ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.