Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ትብብርን እውን ለማድረግ ግንባር ቀደምነቷን አጠናክራ ትቀጥላለች – ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ትብብርን እውን ለማድረግ ግንባር ቀደምነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።
 
በቡሩንዲ ቡጁምቡራ እየተካሄደ በሚገኘው 25ኛው የናይል ቀን እየተሳተፉ የሚገኙት ሚኒስትሩ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ለሩብ ክፍለ ዘመን በዘለቀ ጉዞው ጥሩ ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።
 
ምንምን እንኳን ህጋዊ አካልነት ባያገኝም÷ በተወሰኑ የተፋሰሱ አካባቢዎች የልማት ስራዎችን ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል፡፡
 
በአባል ሀገራት መካከል የውይይት ፎረሞችን በመፍጠር፣ የአቅም ግንባታ ስራዎችን በማከናወን፣ ስለተፋሰሱ ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ አበረታች ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡
 
የተፋሰሱ የእውቀት ምንጭ በመሆን እንዲሁም የናይል ጉዳዮችንና የትብብር አስፈላጊነትን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስተዋወቅ ስራ ማከናወኑን አንስተዋል፡፡
 
እስከአሁን የሽግግር መሳሪያ ብቻ ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው ኢኒሼቲቩ፤ ቋሚ ህጋዊና ተቋማዊ ማእቀፍ የማግኘቱ ጉዳይ በፍጹም ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ አስገንዝበዋል።
 
የናይል ተፋሰስ አባል ሀገራት አስተዋጽኦና ተሳትፎ ቋሚና ወጥ እንዲሆንና በአባል ሀገራት የመንግስታት መቀያየር ምክንያት ተፅዕኖ ውስጥ የማይወድቅ ጠንካራ ተቋም ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል፡፡
ይህ የብር ኢዮቤልዩ በዓል አባል ሀገራት የናይል ተፋሰስ የትብብር ማእቀፍ ስምምነትን በማጽደቅ ወደፊት ለመራመድ ወሳኝ ወቅት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
ኢትዮጵያም የናይል ተፋሰስ ትብብርን እውን ለማድረግ ግንባር ቀደምነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
 
የትብብር ልማትን በተመለከተ በአባል ሀገራት መካከልና በናይል ተፋሰስ የሚገኙ ህዝቦች ከፍተኛ የመልማት ፍላጎት ቢኖርም÷ የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ የልማት አጀንዳ ሊረጋገጥ አለመቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
 
በዝግጅት ሂደት ላይ የሚገኘው የናይል ተፋሰስ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም የናይል ተፋሰስ ህዝቦችን ፍላጎት ለማሟላት ብሎም ህይወታቸውን ለመቀየር መልካም አጋጣሚ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
 
በናይል ተፋሰስ ተጨባጭ ሁኔታ ከውጭ በሚደረጉ የፋይናንስ ድጋፎች ላይ ብቻ በመመርኮዝ ትልልቅ የልማት ስራዎችን ለማከናወን አዋጭ ሆኖ እንደማይታይም ካለፉት የናይል ቤዝን ኢኒሼቲቭ መረዳት እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡
 
ከዚህም አኳያ የውስጥ አቅምን ተጠቅሞ ሀብት በማሰባሰብ የተዘጋጁ የኢንቨስትመንት ፕጀክቶችን መተግበር እንደሚገባ ሚኒስትሩ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
 
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.