Fana: At a Speed of Life!

በቢሾፍቱ ከተማ “የዲጂታል አድራሻ ስርዓት” ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማገዝ እና ዘመናዊ ከተማን ለመገንባት የሚያስችል “የዲጂታል አድራሻ ስርዓት” በቢሾፍቱ ከተማ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡

የዲጂታል አድራሻ ስርዓቱን መርቀው ለቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ያስረከቡት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)÷”የአድራሻ ሥርዓት ሳይኖር የዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት አይታሰብም” ብለዋል፡፡

መንግስት የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለመገንባት ስትራቴጂ ነድፎ እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡

በዚህም የዲጂታል መታወቂያ፣ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶች እንዲሁም የዲጂታል አድራሻ ስርዓት ዝርጋታ ማሳያዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በ73 የኢትዮጵያ ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ያለው የዲጂታል አድራሻ ስርአት“(eDAS)”አስተዳደራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ቀልጣፋ ለማድረግ፣ የከተሞችን ምቾትና ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ዘላቂ የልማት ግቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል፡፡

የዲጂታል አድራሻ ስርዓቱን የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት እንዳለማው መገለጹንም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ በበኩላቸው÷ በቢሾፍቱ ከተማ የተገኘውን ልምምድ በመጠቀም ፕሮጀክቱን በተለያዩ ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሮች አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ እንዲቆዩ አሳስበዋል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.