Fana: At a Speed of Life!

ከ4 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ጌጣ ጌጦችን ሰርቆ በመሰወር የተጠረጠረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ4 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ጌጣ ጌጦችን ሰርቆ በመሰወር የተጠረጠረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

ተጠርጣሪው ወንጀሉን የፈፀመው በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 በአንድ የወርቅ መሸጫ ሱቅ ውስጥ ሲሆን ግለሰቡ ከግል ተበዳይ ጋር ዝምድና ያለው እና የቁጥጥር ስራ እንዲሰራ ሃላፊነት ተሰጥቶት ሲያገለግል መቆየቱ ተገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ ጥር 18 ቀን 20 16 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ሌሎች የወርቅ ቤቱ ሰራተኞች ወደ ቤታቸው በሄዱበት አጋጣሚ ተጠርጣሪው የተለያዩ ካራት ያላቸው እና የዋጋ ግምታቸው 4 ሚሊየን 802 ሺህ 500 ብር የሆነ 675 ግራም ልዩ ልዩ የወርቅ ጌጣጌጦችን ሰርቆ ተሰውሯል፡፡

ከወርቅ በተጨማሪ 150 ሺህ ብር ግምት ያላቸው 500 ግራም የብር ጌጣጌጦችን እና 22 ሺህ ብር ጥሬ ገንዘብ መውሰዱ ተገልጿል፡፡

ግለሰቡ ተለያዩ የክልል ከተሞች በመንቀሳቀስ አድራሻ እየቀየረ ተደብቆ ለመቅረት ቢያስብም በድጋሚ ከአዲስ አበባ ለመውጣት በላምበረት መናኸሪያ ለጉዞ ሲዘጋጅ ከለሊቱ 10 ሰዓት አካባቢ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

ግለሰቡ ከተያዘ በኋላ በተከናወነ ምርመራ የማስፋት ስራ ከተሰረቁት መካከል 552 ግራም የወርቅ እና 189 የብር ጌጣጌጦች በየካ ክፍለ ከተማ ኮተቤ ወረዳ 10 በሚገኝ የአክስቱ መኖሪያ ቤት ኮርኒስ ውስጥ ተደብቆ ተገኝቷል፡፡

እንዲሁም በተጠርጣሪው የባንክ የሂሳብ ቁጥር ውስጥ የሚገኝ ገንዘብም እንዲታገድ ተደርጓል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.