Fana: At a Speed of Life!

27ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 27ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ::
1 .ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የደን ልማት ፣ጥበቃና አጠቃቀም ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡
ሀገራችን ያላትን የደን ሀብት በአግባቡ ለማልማት፣ ለመጠበቅ እና በዘላቂነት ለመጠቀም፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት እንዲሁም የካርበን ክምችትን ወደ አለም አቀፍ ግብይት ስርዓት ለማስገባት የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
2. በመቀጠል ምከር ቤቱ የተወያየው ከዓለም ዐቀፍ የልማት ማህበር ጋር የተፈረሙ 3 የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነቶች ላይ ነው፡፡
ስምምነቶቹ ለዲጂታል መታወቂያ አካታችነትና አገልግሎት አሰጣጥ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ300 ሚሊየንዶላር፣ ለትምህርትና ስልጠና ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የ200 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም ለንግድ ሎጅስቲክስ ማሻሻያ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል የ90 ሚሊየን ዶላር ብድር የሚያስኙ ናቸው::
ምክር ቤቱም ሁሉም ብድሮች ወለድ የማይታሰብባቸው፣ ብድሮቹን በማስተዳደር ረገድ ለሚወጡ ወጪዎች እንዲሁም ጥቅም ላይ ላልዋለው ገንዘብ 1.25% የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልባቸው፣ የ6 ዓመታት የችሮታ ጊዜ ያላቸው እና በ38 ዓመታት ተከፍለው የሚጠናቀቁ እንዲሁም ከሀገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ ረቂቅ አዋጆቹ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
3. አክሎም ምከር ቤቱ ከጣሊያን መንግስት ጋር በተፈረሙ 2 ፋይናንስ ድጋፍ ምምነቶች ላይ የተወያየ ሲሆን የመጀመሪያው ስምምነት ለቦዬ ሐይቅና አካባቢው ዘላቂ ልማት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የ6.5 ሚሊየን ዩሮ ብድር የሚያስገኝ፣ሁለተኛው ስምምነት ለኢነርጂ ዘርፍ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የ83.5 ሚሊየን ዩሮ ብድር የሚያስገኝ ነው::
ብድሮቹ ከወለድ ነጻ ከመሆናቸውም በላይ የ16 ዓመታት የእፎይታ ጊዜ ያላቸው በ30 ዓመታት ተከፍለው የሚጠናቀቁ መሆኑን እና ከአገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጆቹ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
4. ሌላው ምከር ቤቱ የተወያየው ብሔራዊ የእንሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩትን በልማት ድርጅትነት ለማቋቋም የወጣውንደንብ ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ኢንስቲትዩቱ የእንስሳት በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ክትባቶችን እና መድሃኒቶችን፣ በእንስሳት ጤና ረገድ ለሚደረግ ምርምር የሚያገለግሉ ባዮሎጂካሎችንና ሪኤጀንቶችን እንዲሁም ተዛማጅ ግብአቶችን በራስ አቅም ለማምረት የተያዘውን አገራዊ ስትራቴጂ ማሳካት እንዲችል የኢንስቲትዩቱን ካፒታል ማሳደጊያ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም የኢንስቲትዩቱ የተፈቀደ ካፒታል ብር 2.6 ቢሊየን እንዲሆን፣ ደንቡም በነጋሪት ጋዜጣ ከታተመበት ቀን ጀምሮ ስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
5. በተጨማሪም የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት እና የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ተቋማት ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች የሚከፈሉ የአገልግሎት ከፍያዎችን ለመወሰን በቀረቡ ረቂቅ ደንቦች ላይ ምክር ቤቱ ተወይቷል፡፡ ተቋማቱ የሚሰጡዋቸውን አገልግሎቶች ማስፋት፣ የአገልግሎታችውን የጥራት ደረጃ ማሻሻል፣ ብሎም የተጠቃሚውን ማህበረሰብ አቅም ባገናዘበ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት ያወጡትን ወጪ በከፊል መሸፈን እንዲችሉ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ ደንቦች ተዘጋጅተው ቀርበዋል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቦቹ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውሉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
6. ከዚያም ምከር ቤቱ የተወያየው በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ስራዎቻችን ከዘላቂ የልማት እና ብልጽግና ግቦቻችን ጋር እንዲተሳሰሩ፣ ለሰው ህይወት ቅድሚያ የሚሰጡ እንዲሆኑ ለማስቻል ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን፣ የህገ-መንግስታዊ ስርዓታችን እና ሀገራችን ያፀደቀቻቸውን ስምምነቶች ታሳቢ በማድረግ ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤት ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ከጸደቀበት ከዛሬ የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
7. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው በይነ መንግሥታት የልማት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ማቋቋሚያ ማሻሻያ ስምምነትን ለማጽደቅ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡በአባል ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣አካባቢያዊ እና ፖለቲካዊ ውህደት እንዲሁም የድንበር ተሻጋሪ ትብብርን በማፋጠን የአባል ሀገራትን ዘላቂ ልማት ማሳለጥ የሚገባ በመሆኑ የኢጋድ መመሥረቻ ስምምነት ማሻሻያ ጁን 12 ቀን 2023 በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ጸድቋል፡፡
ምክር ቤቱም በተሻሻለው የኢጋድ ማቋቋሚያ ስምምነት ላይ በሰፊው ተወያይቶ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
8. በኢትዮጵያና በጆርዳን መንግስታት መካከል በስራ ስምሪት ዘርፍ የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ ለማፅደቅ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት አጀንዳ ነው፡፡ ስምምነቱ በጆርዳን በተለያዩ የስራ መስኮች የተሰማሩ እና ለወደፊትም ለሚሄዱ ኢትዮጵያውያን የመብት አከባበር ህጋዊ መሰረት እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡
በሁለቱ መንግሥታት መካከል የሚኖራትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በህዝብ ለህዝብ ደረጃ ለማጠናከርም እንደሚያስችል የታመነበት ስምምነት ማስጸደቂያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ስምምነት ላይ በሰፊው ተወያይቶ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
9. በጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የብሮሚን፣ የግራናይት ፣የድንጋይ ከሰል እና የደለል ወርቅ ማድናት ልማትን የተመለከቱ አራት ረቂቅ ስምምነቶች ላይ ነው፡፡
ለምክር ቤቱ የቀረቡት ረቂቅ ስምምነቶች የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለማሟላት የተነደፈውን ስትራቴጂ በማሳካት፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ፣ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበረከቱ፣ እንዲሁም ከአካባቢ ጥበቃ አና ከማህበረሰብ ተጠቃሚነት ረገድ የመንግስትን የፖሊሲ አቅጣጫ የተከተሉ ስምምነቶች መሆናቸውን በማረጋገጥ የማእድን ሚኒስቴር ስምምነቶቹን እንዲፈራረም እና ወደ ስራእንዲገባ በሙሉ ድምጽ ይሁንታ ሰጥቷል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.