Fana: At a Speed of Life!

የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የጀመረበትን ሁለተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ምዕራባውያን መሪዎች ኪየቭ ገቡ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የጀመረበትን ሁለተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከዩክሬን ጋር ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት ምዕራባውያን መሪዎች ኪየቭ ገብተዋል።

ኪየቭ የገቡት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮንደር ሌየን ከምን ጊዜውም በላይ በገንዘብ፣ በምጣኔ ሀብት፣ በወታደራዊ ድጋፍ እና በማበረታታት ረገድ ከዩክሬን ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል፡፡

በሩሲያና ዩክሬን መካከል ጦርነት የተጀመረው ከሁለት ዓመት በፊት በዛሬዋ ዕለት ሲሆን ረጅም እና ደም አፋሳሽ ጦርነት ተካሂዷል።

ባለፈው ዓመት ዩክሬን ግዛቷን ከሩሲያ ለማስመለስ የመልሶ ማጥቃት ሙከራ ብታደርግም በአብዛኛው እንዳልተሳካላት ነው የተገለጸው።

የዩክሬን ጦር ከምስራቃዊቷ አቪዲቭካ ከተማ ለቆ በመውጣት ሩሲያ ባለፈው ዓመት የፈረንጆቹ ግንቦት ወር ባክሙት ግዛትን ከተቆጣጠረች በኋላ ትልቅ የተባለ ድል እንድታስመዘግብ አድርጓታል፡፡

ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ በጦርነቱ ዓለም አቀፍ የገንዘብ እና ወታደራዊ ድጋፍ ከምዕራባውያን አጋሮች እንዲቀጥል ለማድረግ ከባድ ፈተና ገጥሟቸው ቆይቷል።

ይሁን እንጂ ዩክሬን በጥቁር ባህር በሩሲያ የጦር መርከብ ላይ ጥቃት በማድረስ በወደቦቿ ላይ የተጣለባትን እገዳ እንዲያበቃ ማድረጓን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.