Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የታክስ ሕግ ተገዢነት ንቅናቄ እንደሚካሄድ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ19 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ክልላዊ ወጪን ከ75 በመቶ በላይ ለመሸፈን አቅዶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ገለፀ።

ክልላዊ የታክስ ሕግ ተገዢነት ንቅናቄ በነገው እለት በአርባምንጭ እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን÷ ለግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች እውቅናና ሽልማት የመስጠት መርሐግብር እንደሚከናወንም ተነግሯል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ደመቀ÷ ለገቢ አሰባሰብ ሥራ ተግዳሮት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዋናው አብዛኛው ግብር ከፋይ ደረሰኝ አለመስጠቱ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሸማቹም ለከፈለው ገንዘብ ደረሰኝ ጠይቆ እንደማይቀበል ጠቅሰው፤ ግብር በሚሰውሩና በሚያጭበረብሩ አካላት ላይ እየተወሰዱ ላሉ እርምጃዎች ተገቢው ድጋፍ እየተሰጠ እንዳልሆነ አብራርተዋል።

ችግሩን ለመፍታት ቢሮው የአሰራር ስርዓቶችን መፈተሸና ማስተካከያዎችን ማድረግ እንዲሁም ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩንም ሃላፊዋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡

ህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ለገቢ አሰባሰብ ስራው ፍትሀዊነትና ውጤታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ግቡን ለማሳካት ክልላዊ የታክስ ሕግ ተገቢነት ንቅናቄ እንደሚካሄድና በንቅናቄው በማህበረሰቡ ዘንድ የታክስ ግንዛቤን በማሳደግ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በታክስ ሕጉ መሠረት መሰብሰብ የማስቻል አላማ እንዳለውም ተመላክቷል፡፡

በመለሰ ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.