Fana: At a Speed of Life!

በኮልፌ ቀራኒዮና አዲስ ከተማ ክ/ከተሞች ሕዝባዊ ውይይት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮልፌ ቀራኒዮ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ሕዝባዊ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

የውይይት መድረኩ “ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡

በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ እየተካሄደ ባለው መድረክ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና በሚኒስትር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ ተገኝተዋል፡፡

አቶ አረጋ በበኩላቸው መንግሥት ኅብረ ብሔራዊ አንድነትንና ገዥ ትርክቶችን በማጎልበት ለሁለንተናዊ ብልፅግና እንደሚሠራ ገልጸው÷ በሕዝባዊ ውይይቶች የተነሱ ፍላጎቶችና የመልማት ጥያቄዎችን እንደ ግብዓት በመውሰድ በየደረጃው ይፈታል ብለዋል፡፡

የተናጠል ትርክቶችን በመቅረፍ ገዥ ትርክትን ለማጎልበት እንሚሠራም ነው የተናገሩት፡፡

በተመሳሳይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት ሕዝባዊ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማው መድረክ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ እና የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ ተገኝተዋል፡፡

በመድረኩ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚስተዋሉ የተለያዩ ሃሳቦችና ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡

ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ ታሪኮቻችንን አብሮነትንና አንድነትን በሚያፀኑበት አግባብ ልንጠቀምባቸው ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የበርካታ ጸጋዎች ባለቤት መሆኗን ጠቁመው ይህንም ወደ ብልጽግና ለመለወጥ እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በሳሙኤል ወርቃየሁ እና ትዕግስት ብርሃኔ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.