Fana: At a Speed of Life!

በ1 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

በምረቃ ሥነ÷ሥርዓቱ የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኡባህ አደም (ዶ/ር) ተገኝተዋል፡፡

ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ÷ ሆስፒታሉ በከፊል ወደ አገልግሎት መግባቱ በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል የተሻለ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።

በተለይም ድሬዳዋ የምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል መሆኗን ተከትሎ እየጨመረ የሚገኘውን የጤና አገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት የሆስፒታሉ ጠቀሜታ የጎላ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በቀጣይም ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ ወደ አገልግሎት እንዲገባ ሚኒስቴራቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠው÷ ዩኒቨርሲቲውም በጀመረው ጥረቱ መበርታት እንዳለበት አሳስበዋል።

ሆስፒታሉ እስከ 400 የህሙማን አልጋዎች፣ አራት ዋና እና አራት መለስተኛ የቀዶ ጥገና ክፍሎች፣ የማዋለጃ ክፍል፣ የፅኑ ህሙማንና ፋርማሲዎች፣ የጥናት ማዕከላትና ሌሎች ክፍሎችን በውስጡ ማካተቱ ተመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.