Fana: At a Speed of Life!

የእስራኤል ልዑካን በተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመምከር ወደ ኳታር አቀኑ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራኤል ባለስልጣናት በጋዛ የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት ላይ ለመምከርት ወደ ኳታር ማቅናታቸው ተገልጿል፡፡
 
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ደቡባዊ ጫፍ በምትገኘው ራፋህ ላይ ጥቃት ለማድረስ የምትሰነዝረውን ዛቻ ለመግታት በቅርቡ የእርቅ ስምምነት እንድትደርስ ከዋነኛ አጋሯ አሜሪካ ሳይቀር ጫና እየደረሰባት መሆኑ ተመላክቷል።
 
ልዑካን ቡድኑ ከወታደራዊ እና ከሞሳድ የስለላ ድርጅት የተወጣጣ ሲሆን÷ ድርድርን የሚደግፍ የተልዕኮ ማዕከል የመፍጠር ሃላፊነት እንደተጣለበት ተገልጿል።
 
ተልዕኮው ሃማስ እንዲፈቱ የሚፈልጋቸውን የፍልስጤም ታጣቂዎች ማጣራት እና የታገቱትን የመልቀቂያ ውል አካል አድርጎ እንደሚያካትትም ነው የተጠቆመው።
 
ባለፈው ሳምንት ሃማስ ባይካተትበትም የእስራኤል ባለስልጣናት ከአሜሪካ፣ ግብፅ እና ከኳታር ልዑካን ቡድን ጋር በፓሪስ በታጋቾች መልቀቂያ ውል ዙሪያ መምከራቸው ተጠቅሷል፡፡
 
የግብፅ የጸጥታ ምንጮች እንደተናገሩት÷ ፊት ለፊት ባያገናኟቸውም ከእስራኤል እና ከሃማስ የተወጣጡ ልዑካንን ያሳተፈ ድርድር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በኳታር እና በኋላም በካይሮ በአሸማጋዮች በኩል ይደረጋል።
 
ይሁንና ይሄኛውን የድርድር ሁኔታ በተመለከተ እስራኤል ያለችው ነገር እንደሌለና በኳታር በኩልም የተሰጠ መግለጫ አለመኖሩን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.