Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል ጎን ለጎን ደም የመለገሱ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦቦት 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል ጎን ለጎን ደም የመለገሱ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ጥሪ አቀረቡ።

የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ በብሔራዊ ደም ባንክ በመገኘት ደም ለግሰዋል።

ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚህ ወቅት እንዳሉት የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ የደም ለጋሾች ቁጥር ቀንሶ እንደነበር አስታውሰዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ በተደረገው ተከታታይ የንቅናቄ ሥራ በአሁኑ ወቅት ደም የሚለግሱ ሰዎች ቁጥር መሻሻል አሳይቷል ብለዋል።

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ከእለት ወደ ዕለት የለጋሾች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፥ ተግባሩ በሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎችም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

አሁንም ደም የሚያስፈልጋቸው ዜጎቻችን በሕክምና ውስጥ አሉ ያሉት ሚኒስትሯ፥ ከዚህ አንጻር ደም የመለገሱ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይ የኮሮና ቫይረስ ከፈጠረው የጤና ቀውስ አንጻር በአሁኑ ወቅት ደም መለገስ ዋጋው ከፍ ያለ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ዜጎች ደም በሚለግሱበት ወቅት ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት የሚደረጉ ጥንቃቄዎችን ሊዘነጉ እንደማይገባም መክረዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.