Fana: At a Speed of Life!

ሕብረተሰቡ ከሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመራቅ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት ክልል ለመገንባት እንዲረባረብ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የተገኘው አንጻራዊ ሰላም የተሟላ እንዲሆን ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ከሐሰት ፕሮፓጋንዳ ራሱን በማራቅ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት ክልል ለመገንባት በጋራ እንዲረባረብ ጥሪ ቀረበ፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በመግለጫውም በቀጣይ ልማቱን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ሰላምን ለማረጋገጥ ውስጣዊ አንድነትንና የውስጥ ሰላምን የበለጠ ማጽናት ይገባል ብሏል፡፡

የክልሉ መንግሥት መግለጫ ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡-

ሕግ ማስከበር ዋነኛ ግቡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ ነው!

የሕግ የበላይነት መረጋገጥ የአንድን ማኅበረሰብ የተረጋጋ ዘላቂ ሕይወት ለመመስረትና ለመጭውም ትውልድ የሚተርፍ ዐሻራ ለማኖር ወሳኝ ነው።

በግጭት ውስጥ የቆየ ማኅበረሰብ ለሕይወቱ፣ ለንብረቱና አጠቃላይ የኑሮው ዋስትና ስለማይኖረው የዕለት ልብሱንና ጉርሱን ከመሻት አልፎ የዘላቂ ልማት ዓላማን ታሳቢ ያደረገ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ሊሰማራ አይችልም።

ሕገ-ወጥነትንና ሥርዓት አልበኝነት እንደሕዝብ አለመረጋጋትን የሚያስከትል በመሆኑ መቆጣጠር ካልተቻለ ሁሉንም ነገር ደረጃ በደረጃ ከመንግሥትና ከሕዝብ እጅ እንዲወጣ ያደርጋል።

ይህ ሁኔታ እንዳይፈጠር እና ሲፈጠር ለመቆጣጠር መንግሥት የሚጠበቅበትን ሕግ የማስከበር ሥራ ይሠራል።

እዉነታው ይህ ሁኖ እያለ አንዳንድ አጥፊ ቡድኖችና ግለሰቦች የመንግሥትን ሆደ ሰፊነት ቦታ ባለመስጠት በሕዝብ ላይ ያልተገባ ሕገ-ወጥ ተግባር ሲፈጽሙ ይታያሉ።

እነዚህ ቡድኖች እና ግለሰቦች ራሳቸውን ከሕግ በላይ በማድረግ በተለያዩ ቦታዎች ያልተገባ ተግባር ከመፈጸም ባለፈ መንግሥት የዕለት ተዕለት ተግባሩን ለሕዝብ እንዳያደርስ እንቅፋት እየፈጠሩ ቆይተዋል።

በጽንፈኞች መሪ ተዋናኝነት በክልላችን በቅርብ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የዜጎች እንቅስቃሴ የተገታበት፣ የመንግሥት ተቋማት ሥራ የተስተጓጎለበትና የተዘረፉበት፣ ከሁሉ በላይ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የክልላችን ወጣቶች የጽንፈኞች ሐሳብ ተሸካሚ ሁነው የሕይወት ዋጋ የከፈሉበትን ሁኔታ አስተናግደናል።

ይህ ዕኩይ ተግባራቸውም በጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን እና በክልላችን የጸጥታ ኃይል በጋራ በሠሩት ታሪካዊ ተግባር ፍላጎታቸው ሳይሳካ መክኗል። ይሁን እንጅ ይህ አጥፊ ቡድን የራሱን ግፍ እንደቅዱስ ተግባር በመቁጠር የመከላከያ ሠራዊታችን ምት መቋቋም ሲያቅተው የንጹሀንን ካባ ለብሶ ሙሾ ማውረድ ዛሬም የዘለቀው የዕለት ከዕለት ተግባሩ አድርጎታል።

የዚህ ዕኩይ ተግባሩ ዋነኛ ማሳለጫውም ከውጭና ከውስጥ በተዘረጋ የጥፋት ኔትወርክ ተጠቅሞ እየተወሰደበት ያለውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ ሕዝብ ውስጥ በመወሸቅና ራሱን የሕዝብ ብቸኛ ጠበቃ በማስመሰል ማስተጓጎል ነው። የቡድኑ ባህሪም ሲመታ የንጹሀን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ አረመኔያዊ ተግባሩን ሲፈጽም ደግሞ እንደጀብዱ የሚቆጥሩ አጥፊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ማራገብ ነው።

በአሁኑ ወቅት ጽንፈኛ ቡድኑ ሴራው በአደባባይ ተገልጦበት፤ ጉልበቱ ከድቶት አለኝ የሚለውን ገዥ ቦታ ሳይቀር ለመከላከያ ሠራዊታችን እና ለክልላችን የጸጥታ ኃይል በማስረከብ በየጉሬው ተደብቆ ይገኛል። ቡድኑም አንዳንዴ ከተደበቀበት ጉሬ በመውጣት የውጭና የውስጥ ደጋፊዎችን አለሁ ለማለት ብቻ እኩይ ተግባሩን እየፈጸመ ይገኛል።

በክልላችን የተጀመረው ሕግ ማስከበር ሥራ ዋና ዓላማውም የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ታልሞ የሚተገበር በመሆኑ በቀጣይም ሕግ የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። ለዚህም ሕብረተሰቡ ከመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ጎን ሆኖ ድጋፉን አጠናክሮ በመቀጠሉ አመርቂ ውጤቶች ተመዝገበዋል።

በውጤቱም በአብዛኛው የክልላችን አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል።

በተገኘው አንጻራዊ ሰላምም በጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን መሰረተ ልማትና ተቋማት ከመጠገን በተጨማሪ የክልሉን ሕብረተሰብ ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በመሆኑም የተገኘው አንጻራዊ ሰላም የተሟላ እንዲሆን ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ከሀሰት ፕሮፓጋንዳ ራሱን በማራቅ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት ክልል ለመገንባት በጋራ መረባረብ ይኖርበታል። በቀጣይም ልማቱን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ሰላምን ለማረጋገጥ ውስጣዊ አንድነትንና የውስጥ ሰላምን የበለጠ ማጽናት ይገባል!

የአማራ ክልል መንግሥት ኮሚኒኬሽን ቢሮ

ባህር ዳር!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.