Fana: At a Speed of Life!

በ45 ሚሊየን ዶላር የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ማሻሻያ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊደረግ ነው

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተመረጡ 10 ከተሞች የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት መልሶ ግንባታና አቅም ማሻሻያ ፕሮጀክት ቀርፆ ወደ ስራ መግባቱ ተገለፀ፡፡

የፕሮጀክቱ ተግባራዊ መደረግም በዲስትሪቢዩሽን መስመሮች እርጅና ምክንያት በከተሞች አካባቢ እያጋጠመ ያለውን የኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ መሆኑ ተግልጿል፡፡

እንዲሁም ፕሮጀክቱ ቴክኒካል የሃይል ብክነትን ለመቀነስ፣ አዲስ ሃይል ፈላጊ ደንበኞች ለማገናኘት እና የሃይል አቅርቦቱን ጥራት ያለውና አስተማማኝ ለማድረግ የሚረዳ ነው ተብሏል፡፡

የዲስትሪቢዩሽን መስመር መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚደረገው በነቀምት፣ በአምቦ፣ በሱሉልታ፣ በቢሾፍቱ፣ በአሰላ፣ በደብረ ብርሃን፣ በዲላ፣ በሆሳዕና፣ በአሶሳ እና በጅግጅጋ ከተሞች ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 195 አዳዲስ ትራንስፎርመሮችን መገንባት፣ የ1 ሺህ 9 ትራንስፎረመሮች ማሻሸያ እና አቅም ማሳደግ ስራ እና 1 ሺህ 107 ኪሎሜትር የሚሆን የመካከለኛ ቮልቴጅ መስመር ማስፋፊያና ማሻሻያ ስራን የሚያካትት ነው ተብሏል፡፡

የፕሮጀክቱ የገንዘብ ወጪን የአለም ባንክ እንደሚሸፍን የተገለፀ ሲሆን÷ ስራውን ለማጠናቀቅ 45 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መመደቡን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ተቋሙ በአሁኑ ወቅት አለም አቀፍ አማካሪ ቅጥር ያጠናቀቀ መሆኑን እና የፕሮጀክቱን የግንባታ ስራ የሚያከናውኑ አለም አቀፍ ተቋራጮችን የመለየት ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.