Fana: At a Speed of Life!

በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ወደ ግላስጎው አቀና

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ19ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚካፈለው የኢትዮያ ልዑክ ወደ ግላስጎው አቀና፡፡

19ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከፈረንጆቹ መጋቢት 1 እስከ 3 ቀን 2024 በግላስጎው እንደሚካሄድ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያን ወክሎ በውድድሩ ለሚካፈለው የልዑካን ቡድንም ዛሬ ዕኩለ ቀን ላይ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሽኝት ተደርጎለታል፡፡

በሽኝት ሥነ-ሥርዓቱም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ ሌሎችም አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

በውድድሩ ሥድስት ወንድ እና ስምንት ሴት አትሌቶች ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ፡፡

በዚህም መሰረት በሴቶች 800 ሜትር አትሌት ሀብታም ዓለሙ፣ ጽጌ ዱጉማ ሲካፈሉ ወርቅነሽ መሰለ በተጠባባቂነት ተይዛለች።

እንዲሁም በ1 ሺህ 500 ሜትር አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ፣ ድርቤ ወልተጂ እና ብርቄ ኃየሎም ይሳተፋሉ፡፡

ለምለም ኃይሉ፣ ጉዳፍ ፀጋይ እና ሒሩት መሸሻ በ3 ሺህ ሜትር ኢትዮጵያን ሲወክሉ÷ መልክናት ውዱ በተጠባባቂነት ተይዛለች።

በወንዶች 3 ሺህ ሜትር ሰለሞን ባረጋና ጌትነት ዋሌ የተካተቱ ሲሆን÷ ጥላሁን ኃይሌ በተጠባባቂነት ተይዟል።

በሌላ በኩል አትሌት ሳሙኤል ተፈራና ቢኒያም መሐሪ በ1 ሺህ 500 ሜትር ኢትዮጵያን ይወክላሉ።

በ800 ሜትር አትሌት ኤፍሬም መኮንን በብቸኝነት ኢትዮጵያን እንደሚወክል ታውቋል፡፡

በአጠቃላይ ከ133 ሀገራት የተውጣጡ 651 አትሌቶች በውድድሩ እንደሚካፈሉ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.