Fana: At a Speed of Life!

ከ23 ቢሊየን ብር በላይ የመንግስትን ጥቅም ማስጠበቅ መቻሉን የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በግማሽ ዓመት በ3 ሺህ 496 መዛግብት ላይ የፍትሐ-ብሔር ውሳኔ በማሳለፍ ከ23 ቢሊየን ብር በላይ የመንግስትን ጥቅም ማስጠበቅ እንደቻለ የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ።

5ኛው ሀገር አቀፍ የፍትሕ ሚኒስቴርና የክልል ፍትሕ ቢሮ የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃጸም ግምገማ የጋራ መድረክ በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)÷የፍትሕ ዘርፍ መዋቅራዊ ለውጥ ፍኖተ ካርታ በፌዴራልና በክልሎች መካከል ወጥ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ይገመገማሉ ብለዋል።

በመላው ሀገሪቱ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል “የመሠረተ ማኅበረሰብ የፍትሕ ሞዴል ማዕቀፍ” ረቂቅ አዋጅ ለውይይት ቀርቦ ግብዓት እንደሚታከልበትም አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ተክሌ በዛብህ÷በመዲናዋ በግማሽ ዓመቱ በ1 ሺህ 631 የፍትሐ-ብሔር መዝገቦች ክርክር በማድረግ 1 ሺህ 509 የሚሆኑትን በመርታት 581 ሚሊየን ብር የከተማ አስተዳደሩን ጥቅም ማስጠበቅ እንደተቻለ ገልጸዋል።

በፍትሕ ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ደሳለኝ መንግስቴ÷የሕግና ፍትህ፣ የሰብዓዊ መብት ማስከበር፣ የፍትሕ አገልግሎት፣ የፍትሕና ህግ ቋሚ ኮሚቴ ግብረ-መልስ የስድስት ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርቶችን አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የመንግስትን የፍትሐ-ብሔር ጥቅም ለማስጠበቅ በ13 ሺህ 400 መዛግብት ላይ ክርክር እንደተደረገ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.