Fana: At a Speed of Life!

የኔቶ ወታደሮች በዩክሬን የሚሰማሩ ከሆነ ውስብስብ ሁኔታ ሊከተል እንደሚችል ሩሲያ አስጠነቀቀች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) ወታደሮች በዩክሬን የሚሰማሩ ከሆነ ዓለም እጅግ ውስብስብ ሁኔታ ልታስተናግድ እንደሚችል አስጠንቅቃለች።

ሩሲያ ይህን ያለችው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በፓሪስ በተካሄደው የአውሮፓ መሪዎች ስብሰባ ኔቶ በዩክሬን የእግረኛ ወታደራዊ ሀይሉን ሊያሰማራ እንደሚችል መግለፃቸውን ተከትሎ ነው፡፡

በዚህ የተነሳም የሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ኮንስታንቲን ኮሳቼቭ በሰጡት ምላሽ÷ ኔቶ ወታደራዊ ሀይሉን በዩክሬን የሚያሰማራ ከሆነ በሞስኮ ላይ በቀጥታ ጦርነት እንደማወጅ ይቆጠራል፡፡

ይህ የኔቶ ሃሳብ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ እጅግ ውስብስብ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል አስገንዝበው፤ የኔቶን እቅድ ክሬምሊን በዝምታ አታልፈውም ብለዋል፡፡

የአውሮፓ መሪዎች ሩሲያን ለመዋጋት ወታደሮቻቸውን ወደ ዩክሬን ለመላክ ምንም አይነት እቅድ እንደሌላቸው ቢነገርም የምዕራባውያን ልዩ ሀይሎች ግን ከዩክሬን ጦር ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ሩሲያ ገልፃለች፡፡

ሩሲያ ቀደም ሲል ባደረገችው ወታደራዊ ዘመቻ ቅጥረኛ ሰራዊት ስትል በገለፀቻቸውን የውጭ ተዋጊ ሀይሎች ላይ ጥቃት መፈፀሟን የገለፀች ሲሆን በጥቃቱ ከተገደሉ የውጭ ተዋጊዎች ከ60 በላይ የሚሆኑት ፈረንሳይኛ ተናጋሪ እንደነበሩ መግለጿ የሚታወስ ነው፡፡

የፈረንሳይ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ የፈረንሳይ ወታደሮች ለተልዕኮ ወደ ዩክሬን አለመሄዳቸውን ጠቅሶ፤ ከፈረንሳይ ጦር እውቅና ውጭ በበጎ ፈቃደኝነት ኪቭን ለማገዝ የሚዘምቱ ወታደሮች ሊኖሩ ይችላሉ ማለቱን አርቲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.