Fana: At a Speed of Life!

አይኦኤም ከፍልሰት ተመላሽ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) ኢትዮጵያ ከፍልሰት ተመላሽ ዜጎችን ጥበቃና መልሶ ለማቋቋም የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታወቀ፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከአይኦኤም የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ራና ጃበር እና በድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ አቢባቱ ዋኔ ጋር ተወያይተዋል።

ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከል፣ የተመላሽ ዜጎች ጥበቃና በመልሶ ማቋቋም ረገድ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መደበኛ ባልሆነ መልኩ ለስደት የተጋለጡ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው በመመለስ ወደ ቤተሰቦቻቸውና ወደ መጡበት አካባቢ የመመለስ ሥራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ከምንጩ መከላከል ላይ ያተኮሩ ሥራዎች እና ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ምቹ ሀገር እንድትሆን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

ወላጆቻቸውን በስደት ያጡ ህፃናትና ሴቶች ተገቢውን ድጋፍ አግኝተው መልሰው ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ እና ዘላቂ የመጠለያ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላትን ማስፋፋት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ራና ጃበር በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከልና የፍልሰት ተጎጂዎችን በመደገፍና መልሶ በማቋቋም በኩል የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል፡፡

አይኦኤም ኢትዮጵያ የተመላሽ ዜጎችን ጥበቃና መልሶ ማቋቋም ጋር በተያያዘ ለምትሠራው ሥራ እገዛ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.