Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ኬንያ በቀጣናው ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ኬንያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥና የኢኮኖሚ ትብብርን ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የኬንያ ጉብኝትን አስመልክቶ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ÷ “ኢትዮጵያና ኬንያ ረጅም ጊዜ የቆየ የትብብር፣ የአጋርነት እና የወንድማማችነት ህብረት አላቸው” ብለዋል፡፡

ቀደምት መሪዎች በሰሩት ስራ በሀገራቱ መካከል ግጭቶች እንደሌሉ በመግለጽ፤ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በሁለትዮሽ ትብብር ላይ ሰፊ ውይይት ማካሄዳቸውን አስታውሰዋል፡፡

በውይይታቸው በተለይም ቀደም ሲል በአዲስ አበባ የኢትዮ-ኬንያ የሚኒስትሮች ጥምር ምክር ቤት በደረሰው ስምምነት መሰረት ሀገራቱ ሰባት ስምምነቶችን እንደተፈራረሙ አንስተዋል፡፡

ስምምነቱ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በደህንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቅሰው÷ ቀደም ባሉት ጊዜያትም የተፈረሙ ስምምነቶች የሚጠናከሩበት እና የሚሰፉበት ጉዳይ ላይ እንደመከሩ ገልጸዋል፡፡

ሀገራቱ በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ በመሆናቸው ከተለዋዋጩ እና ከአዳጊው የዓለም ሁኔታ ጋር በሚያድግ መልኩ የሁለቱ ሀገራት የደህንነት ሁኔታ መጠናከር በሚችልበት ላይም መምከራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም በቀጣናው እንደስጋት የሚታየው አልሸባብ በሁለቱም ሀገሮች ላይ ጥቃት የሚፈጽም በመሆኑ ይሄንን በጋራ በሚመክቱበት እንዲሁም ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም የኢኮኖሚ ትብብር ግንኙነቱ የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑን አንስተው÷ “በዚህም በዘርፉ ላይ ያለው ግንኙነት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለኬንያ የኤሌክትሪክ ሀይል ለማቅረብ ኬንያም ከኢትዮጵያ ገዝታ ለመጠቀም ከስምምነት ላይ ተደርሶ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮችም ተዘርግተዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የወደብ አማራጮቿን እያሰፋች ነው ያሉት ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)÷ “የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በመንገድ አቅርቦት እንዲሁም በዲጂታል ኢኮኖሚና ደህንነት ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ውይይት አካሂደዋል” ብለዋል፡፡

ድህነትን ለማስወገድ የሀገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከር፣ የአቅም ግንባታ ስራዎችን ማጎልበት እንዲሁም የጥናትና ምርምር ስራዎችን በጋራ ለመስራት የሚያስችል ውይይት መካሄዱንም ተናግረዋል፡፡

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.